ማሕልየ መሓልይ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር። 2 በአፉ አሳሳም ይስመኛል፥ ጡቶችሽ ከወይን ይልቅ ያማሩ ናቸው። 3 የሽቱሽ መዓዛ ከሽቱ ሁሉ መዓዛ ያማረ ነው፥ ስምህ እንደሚፈስስ ሽቱ ነው፤ ስለዚህ ደናግል ወደዱህ። 4 ከወደ ኋላህም ሳቡህ፥ በሽቱህ መዓዛም እንሮጣለን፤ ንጉሡ ወደ እልፍኙ አገባኝ፤ በአንቺ ደስ ይለኛል፥ ሐሤትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ጡቶችሽን እንወዳለን፤ አንቺንም መውደድ የተገባ ነው። 5 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፥ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞንም መጋረጃዎች። 6 ፀሓይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለ ሆንሁ አትዩኝ፤ የእናቴ ልጆች ስለ እኔ ተጣሉ፥ የወይን ቦታዎችንም ጠባቂ አደረጉኝ፤ ነገር ግን የእኔን የወይን ቦታ አልጠበቅሁም። 7 ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፤ በባልንጀሮችህ መንጎች መካከል የተቅበዘበዝሁ እንዳልሆን፥ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ጊዜ ወዴት ትመሰጋለህ? 8 አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ያላወቅሽ እንደ ሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ፥ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞች ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ። 9 ወዳጄ ሆይ፥ በፈርዖን ሰረገሎች እንዳለ ፈረሴ መሰልሁሽ። 10 ጕንጮችሽ እንደ ዋኖስ እጅግ ያማሩ ናቸው፥ አንገትሽም በዕንቍ ድሪ ያማረ ነው። 11 ባለ ብር ጕብጕብ የሆነ የወርቅ ጠልሰም ያድርጉልሽ። 12 ንጉሡ በማዕድ እስከሚቀርብ ድረስ፥ የእኔ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ። 13 ውዴ ለእኔ በጡቶች መካከል እንደሚያርፍ እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። 14 ልጅ ወንድሜ ለእኔ በዐይንጋዲ ወይን ቦታ እንዳለ እንደ አበባ ዕቅፍ ነው። 15 ወዳጄ ሆይ፥ እነሆ፥ ውብ ነሽ፤ እነሆ፥ አንቺ ውብ ነሽ፤ ዐይኖችሽም እንደ ርግቦች ናቸው። 16 ልጅ ወንድሜ ሆይ፥ እነሆ፥ አንተ ውብ ነህ፥ መልከ መልካምም ነህ፤ አልጋችንም ለምለም ነው። 17 የቤታችን ሰረገላ የዝግባ ዛፍ ነው፥ የጣሪያችንም ማዋቀሪያ የጥድ ዛፍ ነው። |