መዝሙር 95 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ከምርኮ በኋላ ቤት በተሠራ ጊዜ። 1 ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፤ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት። 2 እግዚአብሔርንም አመስግኑት፥ ስሙንም ባርኩ፥ ዕለት ዕለትም ማዳኑን አውሩ። 3 ክብሩን ለአሕዛብ፥ ተአምራቱንም ለወገኖች ሁሉ ንገሩ፤ 4 እግዚአብሔር ታላቅ፥ ምስጋናውም ብዙ ነውና፥ በአማልክትም ሁሉ ላይ የተፈራ ነውና። 5 የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዝአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ። 6 እምነትና በጎነት በፊቱ፥ ቅድስናና የክብር ገናናነት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው። 7 የአሕዛብ ወገኖች፥ ለእግዚአብሔር አምጡ፥ ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ፤ 8 ለእግዚአብሔር ለስሙ ክብርን አምጡ፤ መሥዋዕት ያዙ ወደ አደባባዮችም ግቡ። 9 ለእግዚአብሔር በቅድስናው ቦታ ስገዱ፤ ምድር በመላዋ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ትነዋወጣለች። 10 እግዚአብሔር አንደ ነገሠ ለአሕዛብ ንገሩአቸው፥ እንዳይናወጥም ዓለሙን ሁሉ አጸናው፥ አሕዛብንም በቅንነት ይገዛል። 11 ሰማያት ደስ ይላቸዋል፥ ምድርም ሐሤትን ታደርጋለች፤ ባሕር ሞላዋ ትናወጣለች፤ 12 በረሃ በእርስዋም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያደርጋሉ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል፤ 13 ይመጣልና፤ በምድር ላይ ሊፈርድ ይመጣልና፤ እርሱም ዓለምን በጽድቅ አሕዛብንም በቅንነት ይገዛል። |