本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ዮዲት 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዮዲት ትውልድና ተግባር 1 በዚያም ወራት የእስራኤል ልጅ የሰለስዳይ ልጅ፥ የሰላምያል ልጅ፥ የናትናኤል ልጅ፥ የኤልያብ ልጅ፥ የኤልያስ ልጅ፥ የሐቂቆ ልጅ፥ የራወይል ልጅ፥ የጋዴዮን ልጅ፥ የአናንዮ ልጅ፥ የሕልቅያ ልጅ፥ የኦዝያል ልጅ፥ የዮሴፍ ልጅ፥ የሆክስ ልጅ፥ የሜራሪ ልጅ ዮዲት ሰማች። 2 ባልዋም ከነገድዋና ከሀገርዋ የሆነ ምናሴ ነበር፤ የገብስ አዝመራ በደረሰበት ወራትም ሞተ። 3 ነዶ ከሚያስሩ ሰዎች ጋራ በእርሻ ውሏልና ራሱን ምች መታው፤ ታምሞ ተኛ፤ በሀገሩ በቤጤልዋም ሞተ፤ እንደ አባቶቹም በሀገሩ በዶታይምና በበላሞን ባለ ቦታ ቀበሩት። 4 ዮዲትም መበለት ሆና ሦስት ዓመት ከአራት ወር በቤትዋ ተቀመጠች። 5 በቤትዋም ሰገነት ላይ የብሕትውና ክፍል አዘጋጀች፤ በወገቧም ማቅ ታጠቀች፤ የመበለትነት ልብሷንም ለበሰች። 6 በመበለትነትም በኖረችበት ወራት ሁሉ ትጾም ነበር። በሰንበት ዋዜማና በሰንበት፥ በመባቻ ዋዜማና በመባቻ፥ በበዓላትና በእስራኤል የደስታ ቀኖች ካልሆነ በቀር አትበላም ነበር። 7 መልከ መልካምና እጅግ ደመ ግቡ ነበረች፤ ባሏ ምናሴም ብሩንና ወርቁን፥ ሴቶችና ወንዶች አሽከሮችን፥ ከብቶቹንም፥ እርሻውንም ትቶላት ነበር፥ በእነርሱም ላይ ትኖር ነበር። 8 ፈጽማ እግዚአብሔርን ትፈራ ነበርና በእርሷ ክፉ ቃልን የሚናገር አልነበረም። ዮዲትና የእስራኤል ሽማግሌዎች 9 ውኃው ስላለቀ ሰውነታቸው ተጨንቃለችና ሕዝቡ በአለቃቸው ላይ የተናገሩትን ክፉ ነገር ሰማች፤ ዮዲትም ዖዝያን ለሕዝቡ የነገራቸውን ቃል ሁሉ፥ ከአምስት ቀን በኋላም ሀገራቸውን ለአሦር ሰዎች እንዲሰጡ እንደ ማለላቸው ሰማች። 10 ገንዘቧን ሁሉ የምትጠብቅ ሞግዚትዋንም ልካ ዖዝያንን፥ ከብሪኒንና ከርሜኒን፥ የከተማዋንም ሽማግሌዎች ጠራቻቸው። 11 እነርሱም ወደ እርስዋ መጡ፤ እርስዋም “ዛሬ በሕዝቡ ፊት የተናገራችሁት በጎ ነገር አይደለምና በቤጤልዋ የሚኖሩ ሰዎች ሹሞች ሆይ! ስሙኝ እግዚአብሔር በእነዚህ በአምስቱ ቀኖች ባይረዳችሁ ሀገራችሁን ለጠላቶቻችሁ አሳልፋችሁ ትሰጡ ዘንድ በእግዚአብሔርና በእናንተ መካከል የተማማላችሁትን መሐላ በዚህ አጸናችሁ። 12 አሁንም በዚች ቀን እግዚአብሔርን የምትፈታተኑት፥ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የተነሣችሁ እናንተ፥ ምንድን ናችሁ? 13 አሁንም እርሱ እግዚአብሔር ይመረምራል፤ እናንተ ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ የሚያደርገውን አታውቁም። 14 በሰው ልቡና ያለ ረቂቅ ምሥጢርን የማታውቁ፥ የልቡናውንም አሳብ የማታስተውሉ ይህን ሁሉ ያደረገ እግዚአብሔርን እንዴት ትመረምራላችሁ? ልቡናውንስ መርምራችሁ ታውቁ ዘንድ እንዴት ትወዳላችሁ? ምክሩንስ መርምራችሁ ታገኙ ዘንድ እንዴት ትመረምራላችሁ? ወንድሞች ሆይ፥ ለእናንተ አግባባችሁ አይደለም፤ አምላካችን እግዚአብሔርንም አታሳዝኑት። 15 በእነዚህ በአምስቱ ቀኖች ይረዳን ዘንድ ባይፈቅድ በማንኛውም ቀን ቢሆን በፈቀደ ጊዜ ሊያድነን፥ ወይም በጠላቶቻችን ፊት ሊያጠፋን ሥልጣን አለው። 16 እግዚአብሔር እንደ ሰው የሚጨክን አይደለምና እንደ ሰውም የሚቀየም አይደለምና፥ እናንተ አምላካችን እግዚአብሔርን አትፈታተኑት። 17 ነገር ግን ከእርሱ የምትገኝ ድኅነትን ደጅ ጥኑ፤ ቃላችንንም ሰምቶ ይረዳን ዘንድ ይፈቅድ እንደ ሆነ ለምኑት። 18 “በዘመናችን ወይም ዛሬ በቀድሞ ዘመን እንደ ተደረገ ከእኛ መካከል ወገንም ቢሆን፥ ነገድም ቢሆን፥ ከተማም ቢሆን፥ መንደርም ቢሆን በሰው እጅ ለተሠሩ ጣዖታት ለመስገድ የተነሣ የለምና። 19 ስለዚህም ነገር አባቶቻችን ለመበርበርና ለጦር ሆኑ፤ በጠላቶቻቸውም ፊት ጽኑ አወዳደቅን ወደቁ። 20 እኛ ግን ያለእርሱ ሌላ አምላክ አናውቅም፤ ስለዚህ እኛን ወይም ወገኖቻችንን ቸል እንደማይለን በእርሱ እናምናለን። 21 እኛ በተያዝን ጊዜ ይሁዳ ሁሉ ይያዛል፤ ንዋየ ቅድሳታችንም ይዘረፋል፤ በመቅደሱም መርከስ ከአንደበታችን ይመረመራል። 22 የወንድሞቻችን መገደል፥ የሀገራችንም መዘረፍ፥ የርስታችንም ምድረ በዳ መሆን በሚገዙን አሕዛብ ዘንድ በእኛ ላይ ይመለሳል፤ ገንዘብ በሚያደርጉን ፊትም በዚያ የተሰነካከልንና መገዳደሪያ እንሆናለን። 23 መገዛታችንም ያለ ምስጋና ይሆናልና፥ አምላካችን እግዚአብሔር መዋረዳችንን አላየምና። 24 “አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ፥ ለባልንጀሮቻችን ንገሩአቸው፤ እኛን ያዳምጣሉና፥ ልቡናቸውም ወደ እኛ ተሰቅሏልና፥ መሠዊያዉና ቤተ መቅደሱም በእኛ ጸንቶ ይኖራልና። 25 አባቶቻችንን እንደ ፈተናቸው የሚፈትነን አምላካችን እግዚአብሔርን በዚህ ሁሉ እናመስግነው። 26 ለአባቶቻችን ያደረገውን ሁሉ አብርሃምን እንደ ፈተነው፥ ይስሐቅንም እንደ ፈተነው፥ ያዕቆብንም የእናቱን ወንድም የላባን በጎች ሲጠብቅ በሶርያ መስጴጦምያ እንደ ፈተነው አስቡ። 27 እነርሱንም በፈተናቸውና ልቡናቸውን በመረመረ ጊዜ እኛን የበደለን አይደለም፤ እግዚአብሔር የሚቀርቡትን ሰዎች ይቅር ይላቸው ዘንድ ነው እንጂ፥ ሊያጠፋቸው አይደለምና።” 28 ዖዝያንም አላት፥ “የተናገርሽውን ሁሉ በበጎ ልቡና ተናገርሽ፤ ቃልሽንም የሚቃወመው የለም። 29 ጥበብሽ የተሰማው ከዛሬ ጀምሮ አይደለምና፥ ከመጀመሪያው ዘመንሽ ጀምሮ ሰው ሁሉ በጥበብሽ ዐወቀሽ እንጂ፥ የልቡናሽ ተፈጥሮ ደግ ነውና። 30 ነገር ግን ሕዝቡ ፈጽመው ተጠምተዋልና እንዳሉን እናደርግ ዘንድ ዘበዘቡን፤ ልንለውጠው የማይቻለንን መሐላ አመጡብን። 31 አሁንም አንቺ እግዚአብሔርን የምትፈሪ ሴት ነሽና እግዚአብሔር ዝናምን ያዘንምልን ዘንድ፥ ኵሬያችንም ይመላ ዘንድ፥ እንግዲህ ወዲህም እንዳንጠማ ለምኝልን።” 32 ዮዲትም አለቻቸው፥ “ስሙኝ ለልጅ ልጅ የሚነገር ሥራን እሠራለሁ። 33 እናንተ ግን በዚች ሌሊት በበሩ ቁሙ፤ እኔም ከብላቴናዬ ጋር እወጣለሁ፤ ሀገራችንን አሳልፈን ለጠላቶቻችን እንሰጣለን በምትሉበት በእነዚያም ወራቶች የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር በእጄ ይረዳል። 34 እናንተ ግን የምሠራውን ሥራ አትመርምሩኝ፤ እኔ የምሠራው ሥራ እስኪፈጸም ድረስ አልነግራችሁምና።” 35 ዖዝያንና አለቆቻቸውም፥ “በሰላም ሂጂ፤ እግዚአብሔርም በፊትሽ ይሁን፤ ጠላቶቻችንንም ይበቀል” አሏት። 36 ተመልሰውም ወደ ባልንጀሮቻቸው ሄዱ። |