本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ዮዲት 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የቤጤልዋ መከበብ 1 በማግሥቱም ሆሎፎርኒስ ወደ ቤጤልዋ ይጓዙ ዘንድ፥ ቀድመውም የአንባዎቹን መግቢያ ይይዙና የእስራኤልን ልጆች ይዋጓቸው ዘንድ ከእርሱ ጋራ የተሰለፉ ጭፍሮቹንና ወገኖቹን ሁሉ አዘዛቸው። 2 በዚያም ቀን ጽኑዓን አርበኞች የሆኑ ኀይለኞች ሰዎች ሁሉ ወረዱ፤ እነዚያም ጓዝ ከሚጠብቁ ካልከበቡ ከብዙ አርበኞች ሰዎች በቀር መቶ ሰባ ሺህ እግረኞችና ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩ። 3 በቤጤልዋ አጠገብ፥ በአውሎን በውኃው ምንጭ አጠገብ ሰፈሩ፤ የሰፈራቸውም አቆልቋዩ እስከ ዶታይምና ቤጤልዋ ድረስ፥ ወርዱም በአሴዴራሎም አንጻር ከቤጤልዋ እስከ ቅያሞስ ደረሰ። 4 የእስራኤልም ልጆች ብዛታቸውን በአዩ ጊዜ እጅግ ደነገጡ፤ እርስ በርሳቸውም፥ “እነዚህ ሰዎች ዛሬ ምድርን ሁሉ ይሸፍኗታል፤ ተራራም ቢሆን፥ ኮረብታም ቢሆን፥ ቈላም ቢሆን ብዛታቸውን የሚችል የለም” ተባባሉ። 5 ሁሉም መሣሪያቸውን ያዙ፤ ባንባቸውም እሳት አነደዱ፤ በዚያችም ሌሊት ሁሉ ሲጠብቁ አደሩ። 6 በሁለተኛውም ቀን ሆሎፎርኒስ በቤጤልዋ ባሉ በእስራኤል ልጆች ፊት ፈረሶቹን ጫነ። 7 የከተሞቻቸውን መግቢያ ያዩ ዘንድ፥ የውኃቸውንም ምንጭ ይከቡ ዘንድ፥ ወደዚያም አርበኞች ሰዎች ቀድመው ይደርሱና ይከቡ ዘንድ ጕበኞችን ላከ። 8 እርሱም ከሠራዊቱ ጋር ፈጥኖ ሄደ፤ አርበኞች የሆኑ የኤሳው ልጆች አለቆችም ሁሉ የሞዓብ ወገኖች ሹሞች ሁሉና የባሕር ዙሪያ ገዢዎች ወደ እርሱ መጡ። 9 እንዲህም አሉት፥ “አቤቱ በሠራዊትህ ላይ ጥፋት እንዳይሆን ቃላችንን ስማ። 10 እነዚህ የእስራኤል ልጆች ወገኖች በሚኖሩባቸው አንባዎቻቸውና ኮረብታዎቻቸው ነው እንጂ በጦራቸው የሚተማመኑ አይደሉም፤ ለአንባዎቻቸው መውጫ የላቸውምና፤ 11 አቤቱ አሁንም በሰልፍ ሥርዐት አቷጋቸው፤ ከሠራዊትህ አንድ ሰው ስንኳ የሚሞት አይኑር። 12 ነገር ግን አንተ ከሠራዊትህ ጋር በሰፈር ጠብቃቸው፤ አሽከሮችህና የሠራዊትህ አርበኞች ሁሉ ከተራራው በታች የሚፈልቅ የውኃቸውን ምንጮች ሁሉ አጽንተው ይጠብቁ። 13 በቤጤልዋ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ከዚህ ውኃ ስለሚቀዱ ውኃ ጥም ይገድላቸዋል፤ ሀገራቸውንም ለአንተ ያሰገዛሉ፤ ሠራዊቶቻችንና እኛም ላንባቸው ቅርብ ወደ ሆነ ቦታ ወደ ኮረብታቸውም ራስ እንወጣለን ካንባቸው አንድ ሰው ስንኳ የሚወጣ እንዳይኖር በዚያ ሰፍረን እንጠብቃቸዋለን። 14 እነርሱ፥ ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸውም በረኃብ ይጠፋሉ፤ ሳይዋጓቸውም ባገራቸው ጎዳና ይወድቃሉ። 15 ከድተዋልና፥ በሰላምም አልተቀበሉህምና ጽኑ በቀልን ትበቀላቸዋለህ።” 16 በሆሎፎርኒስ ፊትና በሠራዊቱ ሁሉ ፊት ቃላቸው ደስ አሰኘ፤ እንደ ተናገሩም ያደርጉ ዘንድ አዘዘ። 17 የአሞን ልጆች ሠራዊትም ተጓዙ፤ አምስት ሺህ የሚሆኑ የአሦር ሠራዊትም ከእነርሱ ጋር ነበሩ፤ በአውሎኒም ሰፈሩ፤ የእስራኤልንም ልጆች ምንጮችና ውኃቸውን አስቀድመው ያዙ። 18 የኤሳውና የአሞን ልጆችም ወጥተው በዶታይም አንጻር ባሉ ተራሮች ሰፈሩ፤ ከእነርሱም በምኩር ወንዝ ባለ በኩሲ አጠገብ ባለ በኤቄሬቢን አንጻር ወደ ደቡብና ወደ ምሥራቅ ሰዎችን ላኩ። የቀሩት የአሦር ሠራዊቶች ግን በምድረ በዳ ሰፈሩ፤ ሀገሩንም ሁሉ አለበሱት፤ ከዚህም በኋላ ጓዛቸውን ከእነርሱ የሚበዛ የሌለ ሠራዊታቸውንና ብዙ ገንዘባቸውን አጓዙ። የእስራኤላውያን መጨነቅ 19 ጠላቶቻቸው ስለ ከበቧቸው፥ ከመካከላቸውም መውጫ ስለሌላቸው ሰውነታቸው ተጨንቃለችና የእስራኤል ልጆች ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 20 አሦራውያንም ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ጋር አርበኞቻቸውም በፈረሶችና በሰረገላ የተቀመጡ ሰዎችም ከበዋቸው ሠላሳ አራት ቀን ተቀመጡ፤ በቤጤልዋ የሚኖሩ ሰዎችም በዕቃቸው ያለ ውኃቸው ሁሉ አለቀ። 21 የሚጠጡት ላንድ ቀን የሚያረካቸው ውኃ አልነበራቸውም፤ በመስፈሪያ እየመጠኑ ወደ መጠጣትም ተመለሱ። 22 ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው፥ ጐልማሶቻቸውም ተጨነቁ፤ በውኃ ጥም አለቁ፤ በከተማውም አደባባይና በበሩ ጎዳና ወደቁ፤ ከዚህም በኋላ ምንም ኀይል አልነበራቸውም። 23 ሕዝቡ ሁሉ፥ ጐልማሶችና የከተማው አለቆችም፥ ልጆችና ሴቶችም ወደ ዖዝያን ተሰበሰቡ፤ ቃላቸውንም አሰምተው ጮኹ። በአለቆቻቸውም ፊት እንዲህ አሉ፦ 24 “በእኛ ላይ ታላቅ ጉዳትን ታደርሱብን ዘንድ ከአሦር ሰዎች አሽከሮች ጋራ በሰላም በጎ ነገር ባልተናገራችሁ በእናንተና በእኛ መካከል እግዚአብሔር ይፍረድ። 25 አሁንም የሚረዳን አጣን፤ በፊታቸውም በውኃ ጥምና በጽኑ ጥፋት እንጠፋ ዘንድ እግዚአብሔር በእጃቸው ጣለን። 26 አሁንም ተገዙላቸው፤ ይዘርፉም ዘንድ ከተሞቻችሁን ሁሉ ለሆሎፎርኒስ ወገኖችና ሠራዊት አሳልፋችሁ ስጧቸው። 27 ሰውነታችን እንድትድን፥ የልጆቻችንንም ሞት በዐይኖቻችን እንዳናይ በውኃ ጥም ከምንሞት ቢዘርፉንና ብንገዛላቸው ይሻለናልና፥ የሚስቶቻችንና የልጆቻችን ሰውነትም አልቃለችና። 28 እነሆ፥ ዛሬ በዚች ቀን ይህን ነገር እንዳታደርጉ ሰማይንና ምድርን እንዳባቶቻችን ኀጢአትና እንደ ኀጢአታችን የሚፈርድብን ያባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔርን እናዳኝባችኋለን።” 29 በማኅበሩም መካከል ጽኑ ልቅሶ ሆነ፤ ሁሉም በአንድነት አለቀሱ፤ ቃላቸውንም አሰምተው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 30 ዖዝያንም አላቸው፥ “ወንድሞቻችን ሆይ! ሁልጊዜ በመከራው የሚጥለን አይደለምና ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ቸርነቱን እስኪመልስልን ድረስ እመኑ፤ ዳግመኛም አምስት ቀን ታገሡ። 31 እነዚህ አምስት ቀኖች ካለፉ በኋላ ረድኤቱ ካልመጣልን እንደ ተናገራችሁት እናደርጋለን።” 32 ሕዝቡንም ወደየሰፈራቸው በተናቸው፤ እነርሱም ወደ ከተማቸው ግንብና አንባ ሄዱ፤ ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውንም ወደ ቤታቸው ላኩ፤ በከተማም ፈጽመው የተጨነቁ ነበሩ። |