本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ዮዲት 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አክዮር ለእስራኤል ተላልፎ መሰጠቱ 1 ከዚህ በኋላ በሸንጎው ዙሪያ ያሉ እነዚያ ሰዎች ዝም ባሉ ጊዜ የአሦር ሠራዊት አለቃ ሆሎፎርኒስ አክዮርን በፍልስጥኤም ወገኖችና በሞዓብ ልጆች ሁሉ ፊት እንዲህ አለው፦ 2 “አንተ የኤፍሬም ምንደኛ አክዮር! ዛሬ ትንቢት ትናገርልን ዘንድ እግዚአብሔር ያጸናቸዋልና የእስራኤልን ልጆች አትውጓቸው ትለን ዘንድ አንተ ማን ነህ? ያለ ናቡከደነፆርስ እግዚአብሔር ማን ነው? 3 እርሱ ኀያላኑን ልኮ ከገጸ ምድር ፈጽሞ ያጠፋቸዋል፤ አምላካቸውም አያድናቸውም፤ እኛም የናቡከደነፆር ባሮች እንደ አንድ ሰው እናጠፋቸዋለን፤ በእነርሱ እንረግጣቸዋለንና የፈረሶቻችንንም ኀይል ሊቋቋሙ አይችሉም። 4 ተራሮቻቸውም በደማቸው ይሰክራሉ፤ የልጆቻቸውም ሬሳ ይበዛል፤ የዓለሙ ሁሉ ጌታ ንጉሡ ናቡከደነፆር አጠፋቸዋለሁ ብሏልና ቃሉ ሐሰት እንዳይሆን ከዚህ ዓለም ፈጽመው ይጠፋሉ እንጂ በፊታችን በእግራቸው አይቆሙም። 5 “ዛሬ በኀጢአትህ ይህን የተናገርህ የአሞን ምንደኛ አክዮር፥ አንተ ግን ከግብፅ ሀገር የወጡ እስራኤልን ተበቅዬ እስካጠፋቸው ድረስ ከዚህ ቀን ጀምሮ እንግዲህ ወዲህ ፊቴን አታየውም። 6 የዚያን ጊዜ የጭፍራዎችና የወገኖች ጦር በጎንህ ይገባል፤ ከሬሳዎቻቸውም ጋራ ትወድቃለህ። 7 በተመለስሁም ጊዜ ባሮች ወደ አንባቸው ይወስዱሃል፤ ባቀበቱም ካሉ ከተሞቻቸው ባንዲት ከተማ ያኖሩሃል። 8 እስካጠፋቸውም ድረስ አይገድሉህም። 9 እንደማንችላቸው በልብህ ትታመናለህና ፊትህ አይውደቅ፤ እኔ ተናግሬአለሁና፤ ከቃሌም የሚወድቅ የለምና።” 10 ሆሎፎርኒስም በፊቱ በድንኳኑ ውስጥ የሚቆሙ አሽከሮቹን አክዮርን ይዘው ወደ ቤጤልዋ ይወስዱት ዘንድ፥ ለእስራኤልም ልጆች እርሱን ይሰጧቸው ዘንድ አዘዛቸው። 11 አሽከሮቹም ይዘው ከሰፈሩ ውጭ ወደ ምድረ በዳ ወሰዱት፤ ከምድረ በዳውም መካከል ወደ ተራራማው ሀገር ሄዱ፤ ከዚህም በኋላ በቤጤልዋ በታች ወዳሉ ምንጮች ደረሱ። 12 የዚያችም ሀገር ሰዎች ባዩአቸው ጊዜ መሣሪያቸውን ይዘው ከከተማ ወደ ተራራው ራስ ሄዱ። ወንጭፍ የያዙ ሰዎችም ሁሉ መግቢያውን ጠበቁ፤ በላያቸውም መርግ ጣሉ። 13 የአክዮርንም እግር ብረት ፈቱት፤ በተራራውም በታች አሰሩት፤ በዚያም በተራራው በታች ጣሉት፤ ትተውትም ወደ ጌታቸው ተመለሱ። 14 የእስራኤልም ልጆች ከአንባቸው ወርደው ወደ እርሱ ሄዱ፤ ፈትተውም ወደ ቤጤልዋ ወሰዱት። 15 በዚያም ወራት የከተሞቻቸው አለቆች በነበሩት ከነገደ ስምዖን በሚካ ልጅ ኦዝያስና በጎቶንያ ልጅ በክብሪስ፥ በመልክያል ልጅ በከርሚስም ዘንድ አስቀመጡት። 16 በከተሞቻቸውም ያሉ አለቆችን ሁሉ ጠሩ፤ ሴቶቻቸውና ጐልማሶቻቸውም ሁሉ ሮጠው ወደ ሸንጓቸው ሄዱ፤ አክዮርንም በሁሉ መካከል አቆሙት፤ ኦዝያስም የተደረገውን ሁሉ ጠየቀው። 17 እንደ ዶለቱና በአሦር ሠራዊት አለቆች መካከል ነገራቸውን ሁሉ እንደ ተናገሩ፥ ሆሎፎርኒስም በእስራኤል ወገኖች ላይ በትዕቢት እንደ ተናገረ መልሶ የሆሎፎርኒስን ነገር ሁሉ ነገራቸው። 18 ሕዝቡም ሁሉ በግንባራቸው ወድቀው ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ እንዲህም እያሉ ጸለዩ፦ 19 “አቤቱ የሰማይ አምላክ ሆይ፥ ትዕቢታቸውን ተመልከት፤ የወገኖቻችንንም መከራ አይተህ ይቅር በል፤ በዚችም ቀን ወደ መቅደስህ ተመልከት።” 20 አክዮርንም ደስ አሰኙት፤ ፈጽመውም አከበሩት። 21 ኦዝያስም ከተሰበሰቡበት ወስዶ ወደ ቤቱ አገባው፤ ለሽማግሌዎችም በዓልን አደረጉ፤ ይረዳቸውም ዘንድ የእስራኤልን አምላክ በዚያች ሌሊት ሁሉ ለመኑት። |