本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ዮዲት 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሆሎፎርኒስ በእስራኤል ላይ ለመዝመት የጠራው ስብሰባ 1 “የእስራኤል ልጆች ለሰልፍ ተዘጋጁ፤ የኮረብታቸውንም በሮች ዘጉ። የአምባውንም ራሶች አጠሩ፤ መንገዱንም ጐፃጕፅ አደረጉ” ብለው ለአሦር ሠራዊት አለቃ ለሆሎፎርኒስ ነገሩት። 2 እርሱም ፈጽሞ ተቈጣ፤ የሞአብን አለቆችና የአሞንን ሹሞች፥ በባሕር ዙሪያ ያሉ ገዢዎችንም ጠራቸው። 3 እንዲህም አላቸው፥ “የከነዓን ልጆች ሆይ! ንገሩኝ፤ በተራሮች የሚኖሩ እነዚህ ወገኖች ምንድን ናቸው? በከተሞች የሚኖሩ፥ ሠራዊታቸውም ብዙ የሆኑ እኒያስ ወገኖች ምንድን ናቸው? ጽናታቸውስ ምን ያህል ነው? በእነርሱስ ላይ የነገሠ ንጉሥ ማን ነው? ወይስ ሹማቸው? ወይስ አለቃቸው ማን ነው? 4 በምዕራብ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ጋር ይቀበሉኝ ዘንድ እንዴት አልመጡም?” የአክዮር ንግግር 5 የአሞን ልጆች ሹም አክዮርም እንዲህ አለ፥ “ከእኔ ከባርያህ አንደበት ይህን ነገር ስማ፤ ከእኔ ከባሪያህ አንደበት ሐሰት ነገር አይወጣምና፥ በእነዚህ አንባዎች፥ በአቅራቢያህም ስለሚኖሩ ስለእነዚህ ወገኖች እውነት ነገርን እነግርሃለሁ። 6 እነዚህ ወገኖች ከከላውዴዎን መጡ። 7 በከላውዴዎን ሀገር የሚኖሩ የአባቶቻቸውን ጣዖቶች ያመልኩ ዘንድ አልወደዱምና አስቀድመው በመስጴጦምያ ይኖሩ ነበረ። 8 የወገኖቻቸውንም መንገድ ትተዋልና ላወቁት ከጣዖቶቻቸው ፊት ላወጣቸው ለሰማይ አምላክ ለእግዚአብሔርም ሰግደዋልና ወደ መስጴጦምያ ሸሽተው በዚያ ብዙ ዘመን ኖሩ። 9 ፈጣሪያቸውም ከተሰደዱበት ሀገር ይወጡና ወደ ከነዓን ይሄዱ ዘንድ አዘዛቸው፤ በዚያም ብዙ ዘመን ኖሩ፤ ብርንና ወርቅን፥ ብዙ ከብቶችንም ፈጽመው አበዙ። 10 ረኃብ በከነዓን ሀገር ሁሉ ጸንትዋልና ወደ ግብፅ ወረዱ፤ በዚያም እየተመገቡ ኖሩ፤ በዚያም በዝተው ሞሉ፤ ለወገኖቻቸውም ቍጥር አልነበራቸውም። 11 የግብፅ ንጉሥም በጠላትነት ተነሣባቸው፤ ተተነኰለባቸውም፤ መከራም አጸናባቸው፤ ጡብ በማሠራትም ገዛቸው፤ ባሮችም አደረጋቸው። 12 ወደ አምላካቸውም ጮኹ፤ እርሱም መድኀኒት በሌለው መቅሠፍት የግብፅ ሀገርን ሁሉ አጠፋ፤ ግብፃውያንም ከፊታቸው አስወጡአቸው። 13 እግዚአብሔርም በፊታቸው የኤርትራን ባሕር አደረቃት። 14 ወደ ሲና ተራራና ቃዴስ በርኔ ወሰዳቸው፤ በምድረ በዳ የሚኖሩትንም ሁሉ አወጣቸው። 15 በአሞራውያን ሀገርም ኖሩ፤ የሐሴቦንንም ሰዎች ሁሉ በኀይሉ አጠፋ ዮርዳኖስንም ተሻግረው ተራራማውን ሀገር ሁሉ ወረሱ። 16 ከናኔዎንን፥ ፌርዜዎንን፥ ኢያቡሴዎንን፥ ሴኬምን፥ ጌርጌሴዎንንም ሁሉ ከፊታቸው አስወጣቸው፤ በዚያም ብዙ ዘመን ኖሩ። 17 “በፈጣሪያቸውም ፊት ባልበደሉ ጊዜ መልካም ነገር ሁሉ ሆነላቸው፤ በደልን የሚጠላ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ነበረና። 18 ያዘዛቸውን ሥርዐት በተዉ ጊዜ ግን ፈጽሞ በብዙ ጦር አጠፋቸው፤ ወደ ባዕድ ሀገርም ተማረኩ፤ የፈጣሪያቸው ማደሪያ ቤተ መቅደስም ፈረሰ፤ ምድረ በዳም ሆነ፤ ከተሞቻቸውንም ጠላቶቻቸው ያዙባቸው። 19 ዛሬ ግን ወደ ፈጣሪያቸው ተመለሱ፤ ከተበተኑበትም ሀገር ከዚያ ተሰበሰቡ፤ ቤተ መቅደስ ባለበት በኢየሩሳሌም ኖሩ፤ ምድረ በዳም ነውና በተራራው ኖሩ። 20 አሁንም አቤቱ ጌታዬ እነዚህ ወገኖች በደል እንዳለባቸው፥ ፈጣሪያቸውንም በድለው እንደ ሆነ ይህ መሰናክላቸው ነውና አንድ ጊዜ እናረጋግጥ፤ ከዚያ በኋላ ወጥተን እንዋጋቸዋለን። 21 በእነዚህ ወገኖች በደል ከሌለባቸው ግን ጌታዬ እለፋቸው፤ እነሆ ጌታቸው ያጸናቸው ይሆናል፤ ወይም አምላካቸው ይቆምላቸው ይሆናል፤ እኛም በሀገሩ ሁሉ ኀፍረት እንሆናለን።” 22 ከዚህ በኋላ አክዮር ይህን ነገር ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ በሰፈሩ ዙሪያ የቆሙ ወገኖች ሁሉ አንጐራጐሩ፤ የሆሎፎርኒስ ሹሞች፥ በባሕር ዙሪያና በሞዓብ የሚኖሩ ሰዎችም ሁሉ “አክዮርን እንግደለው” አሉ። 23 “ከጽኑ አርበኛ ጋር ይዋጉ ዘንድ ብርታትና ኀይል የሌላቸውን ወገኖች የእስራኤልን ልጆች የምንፈራቸው አይደለም። 24 ስለዚህ ግን ጌታችን ሆሎፎርኒስ ሆይ፥ እንዝመት፤ እነርሱም ለጭፍራዎችህ ሁሉ ምግብ ይሆናሉ” አሉ። |