本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ዮዲት 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አይሁድ ራሳቸውን ለመከላከል ያደረጉት ዝግጅት 1 በይሁዳ የሚኖሩ የእስራኤል ልጆች የአሦር ንጉሥ የናቡከደነፆር ቢትወደድ ሆሎፎርኒስ በአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ፥ አውራጃዎቻቸውን ሁሉ እንዳጠፋ፥ እነርሱንም እንዳጠፋቸው ሰሙ። 2 ከመቅረቡም የተነሣ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ አምላካቸው ስለ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፈጽመው ፈሩ። 3 ከይሁዳ የተመረጡ ወገኖችም ሁሉ በቅርቡ ከምርኮ ከተመለሱ በኋላ ተሰብስበው ነበርና ምሥዋዑንና ንዋየ ቅድሳቱን፥ ቤተ መቅደሱንም ከረከሰ በኋላ አነጹት። 4 ስለዚህም ወደ ሰማርያ አውራጃዎችና ወደ ቆና፥ ወደ ቤቶሮንና ወደ ቤልሜን፥ ወደ ኢያሪኮና ወደ ኮባ፥ ወደ ኤሦራና ወደ ሳሌም ሸለቆ ሁሉ ላኩ። 5 ከፍ ያሉ የተራራዎቻቸውንም ጫፎች ያዙ። በሚኖሩባቸው መንደሮችም መሸጉ። አዝመራቸውም ቀደም ብሎ ተሰብስቦ ነበርና ለጦርነት ስንቅን አዘጋጁ። 6 በዚያም ወራት በኢየሩሳሌም የሚኖር የካህናቱ አለቃ ኢዮአቄም በዶታይም አጠገብ ባለች ምድረ በዳ፥ በኤስድራሎም አንጻር ባለች በቤጦሜስቴምና በቤጤልዋ ለሚኖሩ ሰዎች ጻፈ። 7 በዚያም በይሁዳ ላይ መግቢያ ስለአለና መግቢያውም ለሁለት ሰዎች መተላለፊያ ብቻ ነው እንጂ ጠባብ ስለ ሆነ የሚወጡትን ለመከላከል የአንባዎቹን መግቢያ አጽንታችሁ ጠብቁ ብሎ ጻፈ። የእስራኤል ጸሎት 8 የእስራኤልም ልጆች ታላቁ ካህን ኢዮአቄምና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የእስራኤል ወገኖች አለቆች ሁሉ እንዳዘዙአቸው አደረጉ። 9 የእስራኤልም ልጆች ከፍ ባለ ቃል ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ሰውነታቸውንም በጽኑ ኀዘን አሳዘኑ። 10 እነርሱም ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው፥ ከብቶቻቸውም፥ ምንደኛውና ስደተኛው ሁሉ፥ በዋጋም የተገዛው ሁሉ ማቅ ለብሰው አለቀሱ። 11 የእስራኤልም ወገኖች ሁሉ ሚስቶቻቸውና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ልጆቻቸውም በቤተ መቅደስ ደጃፍ ወደቁ፤ በራሳቸውም ትቢያ ነሰነሱ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ማቃቸውን አነጠፉ፤ መሠዊያውንም ማቅ አለበሱ። 12 ልጆቻቸውን እንዳይነጠቁ፥ ሚስቶቻቸውን እንዳይማረኩ፥ የርስታቸው ከተሞችም እንዳይጠፉ፥ መቅደሳቸውንም እንዳያረክሱ፥ ለአሕዛብም መዘበቻ እንዳያደርጉት ወደ እስራኤል አምላክ በአንድነት ፈጽመው ጮኹ። 13 እግዚአብሔርም መከራቸውን አይቶ ልመናቸውን ሰማ፤ ሕዝቡም በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር መቅደስ ፊት ብዙ ቀን ጾሙ። 14 በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ ታላቁ ካህን ኢዮአቄምና ካህናቱ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ የሚሠሩ ሰዎች በወገባቸው ማቅ ታጠቁ፤ የዘወትሩን መሥዋዕት፥ የስእለቱንና ሕዝቡ በፈቃድ የሚያቀርቡትን መሥዋዕት አገቡ። 15 በራሳቸውም ዐመድ ነሰነሱ፤ በፍጹም ኀይላቸውም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ “የእስራኤልንም ወገን በምሕረት ተመልከት” አሉ። |