本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ዮዲት 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዮዲት የምስጋና መዝሙር 1 ዮዲትም ይህቺን የምስጋና መዝሙር በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ትዘምር ጀመረች፤ ሕዝቡም ሁሉ ይህቺን የምስጋና መዝሙር ከእርስዋ ቀጥለው ዘመሩ። 2 ዮዲትም አለች፥ “አምላኬን በከበሮ አመስግኑት፤ ለጌታዬም በጸናጽል ዘምሩለት፤ በገና እየደረደራችሁ አመስግኑት፤ በምስጋና ከፍ ከፍ አድርጉት። ስሙንም ጥሩ፤ 3 እግዚአብሔር በጦርነት ጦርን ያሸንፋልና። 4 ስሙም እግዚአብሔር ነው፤ ሠራዊቱም በሕዝቡ መካከል ነው፤ ከሚያሳድዱኝም ሰዎች እጅ አዳነኝ። 5 አሦራውያን በመስዕ በኩል ከተራራው ወጡ፤ ከብዙ ሠራዊቶቻቸውም ጋር ወጡ፤ በብዛታቸውም ፈሳሹን ዘጉ። ፈረሶቻቸውም ኰረብታውን ሸፈኑት። 6 አውራጃችንን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ፥ ጐልማሶቻችንንም በጦር ይገድሉ ዘንድ፥ ሕፃኖቻችንንም በምድር ላይ ይፈጠፍጡ ዘንድ፥ ወንዶች ልጆቻችንንና ቆነጃጅቶቻችንን ይማርኩ ዘንድ አዝዘው ነበር። 7 ነገር ግን ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር በሴት እጅ አጠፋቸው። 8 አርበኛቸው በጐልማሳ እጅ ድል አልተነሣምና፥ የጤጣኖስ ልጆችም ያጠፉት አይደሉምና። ታላላቁ አርበኞችም ድል አልነሡትም፤ ነገር ግን የሜራሪ ልጅ ዮዲት በደም ግባቷ አጠፋችው። 9 የመበለትነቷንም ልብስ በእስራኤል ዘንድ ስለሚጨነቁት ሰዎች ስትል ተወች። 10 ፊትዋንም ሽቱ ተቀባች፤ ጠጕርዋንም ተሠርታ ሰርመዴ አደረገች፥ እርሱንም ለማሳት የተልባ እግር ልብስን ለበሰች። 11 ጫማዎችዋም ዐይኖቹን በዘበዙ፤ ደም ግባትዋም ሰውነቱን ማረከች፤ ሰይፍም በአንገቱ አለፈ። 12 ከመደፋፈርዋም የተነሣ የፋርስ ሰዎች ደነገጡ፤ ከመጨከንዋም የተነሣ የሜዶን ሰዎች ፈሩ። 13 ያንጊዜ የተጨነቁ ወገኖች ደስ ብሏቸው ደነፉ፤ የእኔ ደካሞች በታላቅ ድምፅ ጮኹ፤ እነዚያም ደንግጠው ነበር፤ እነዚህም ድምፃቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ፤ እነዚያም ደንግጠው ሸሹ፤ 14 የሴቶች ልጆች ልጆችም አሳድደው ወጓቸው፤ ጐልማሶቻችንም አቈሰሏቸው፤ በጌታዬም ጦርነት ጠፉ። 15 ለእግዚአብሔር መዝሙር እዘምራለሁ፤ አዲስ መዝሙር እዘምራለሁ፤ 16 እግዚአብሔር ሆይ፥ ገናና ነህ፤ እጅግም ክቡር ነህ፥ በኀይልህም የተደነቅህ ነህ። 17 ፍጥረትህ ሁሉ ለአንተ ይገዛሉ፤ አንተ አዘዝህ፤ እነርሱም ተፈጥረዋልና፤ መንፈስህን ላክህ፤ እነርሱም ታነጹ፥ ለቃልህም የማይታዘዝ የለም። 18 ተራሮች ከውኆች ጋር ከመሠረቶቻቸው ይነዋወጣሉና፤ ዐለቱም ከገጸ መዓትህ የተነሣ እንደ አደሮ ማር ይቀልጣልና፥ ዳግመኛም የሚፈሩህን ይቅር በላቸው። 19 መሥዋዕቱ ሁሉ ለበጎ መዓዛ አይበቃምና፥ ስቡም ሁሉ ከቍርባንህ ያንሣልና። እግዚአብሔርን የሚፈራው ሰው ግን ሁልጊዜ ገናና ነው። 20 በወገኖች ላይ በጠላትነት ለሚነሡ ለአሕዛብ ወዮላቸው፤ ሁሉን ቻይ እግዚአብሔርም በፍርድ ቀን ይበቀላቸዋል። 21 በሥጋቸውም እሳትና ትልን ይልክባቸዋል፤ በመከራውም ለዘለዓለሙ ያለቅሳሉ።” 22 ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰገዱ፤ ሕዝቡም ራሳቸውን ባነጹ ጊዜ የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና የፈቃድ ቍርባናቸውን፥ ስጦታቸውንም አቀረቡ። 23 ዮዲትም ሕዝቡ የሰጧትን የሆሎፎርኒስን ገንዘብ፥ ከመኝታ ቤቱም የወሰደችውን የራስጌውን ሰይፍ ለመታሰቢያ ለእግዚአብሔር ሰጠች። 24 ሕዝቡም በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ ፊት ሦስት ወር ደስታ አደረጉ፤ ዮዲትም ከእነርሱ ጋር ተቀመጠች። 25 ከእነዚያም ወራት በኋላ ሰው ሁሉ ወደ ርስቱ ተመለሰ፤ ዮዲትም ወደ ቤጤልዋ ተመልሳ በንብረቷ ኖረች፤ በዘመኗም በሀገሩ ሁሉ የከበረች ሆነች። 26 የሚፈልጓትም ብዙዎች ነበሩ፤ ባሏ ምናሴ ሞቶ በወገኖቹ ዘንድ ከተቀበረ ጀምሮ በሕይወት ዘመኗ ሁሉ በግብር ያወቃት ሰው የለም። 27 ፈጽማም በክብር ገነነች። 28 በባሏ በምናሴም ቤት እስክታረጅ ድረስ ኖረች፤ ዕድሜዋም መቶ ዐምስት ዐመት ነበር፤ ያችንም ብላቴናዋን ነጻ አወጣቻት፤ በቤጤልዋ ሞታ በባሏ በምናሴ ዋሻ ተቀበረች፤ 29 የእስራኤልም ወገኖች ሰባት ቀን አለቀሱላት፤ ከመሞትዋም በፊት ገንዘብዋን ለባልዋ ለምናሴ አቅራቢያና ለእርሷ አቅራቢያ ለሆኑ ዘመዶችዋ አካፈለች። 30 የእስራኤልንም ልጆች በዮዲት ዘመን፥ ዳግመኛም እርስዋ ከሞተች በኋላ ለብዙ ዘመን ያስፈራቸው አልነበረም። |