本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ዮዲት 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አሦራውያን ደንግጠው መሸሻቸው 1 በሰፈርም የነበሩ ሰዎች በሰሙ ጊዜ ስለ ተደረገው ነገር ደነገጡ፤ 2 ፍርሀትና እንቅጥቅጥም ያዛቸው፤ ከባልንጀራውም ጋር የቆመ ሰው አልነበረም። ነገር ግን ሁሉም ደንግጠው ወደ ምድረ በዳውና ወደ ተራራማው ሀገር በአንድነት ሸሹ። 3 እነዚያም በቤጤልዋ ዙሪያ፥ በሰፈሩና በተራራማው ሀገር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ተሸብረው ሸሹ፤ ያንጊዜም አርበኞች የሆኑ የእስራኤል ወንዶች ልጆች ሁሉ ተነሥተው ተከተሏቸው። 4 ዖዝያንም ስለ ሆነው ሁሉ ይናገሩ ዘንድ፥ ሁሉም ይረዱ ዘንድ፥ ጠላቶቻቸውንም ተከትለው ያጠፏቸው ዘንድ፥ ወደ ቤጦምስታምና ወደ ቢቤ፥ ወደ ኮቤና ወደ ኮላ ወደ እስራኤልም አውራጃ ሁሉ ላከ። 5 የእስራኤልም ልጆች በሰሙ ጊዜ ሁሉም በአንድነት እስከ ኮቤ ድረስ ተከትለው አጠፏቸው፤ በጠላቶቻቸው ሰፈር የሆነውን ነገር ነግረዋቸዋልና ከኢየሩሳሌምና ከአውራጃዋ ሁሉ የመጡ ሰዎች እንደዚሁ አጠፏቸው፤ ከገሊላና ከገለዓድም የመጡ ሰዎች አባረሯቸው፤ ከደማስቆና ከአውራጃዋም እስኪሻገሩ ድረስ ታላቅ ሰልፍ አድርገው አጠፏቸው። 6 በቤጤልዋም የሚኖሩ ሰዎች ወደ አሦራውያን ሰፈር ወርደው ገንዘባቸውን በዘበዝዋቸው፤ ፈጽመውም ከበሩ። 7 ከዚህ በኋላም የእስራኤል ልጆች ከተዋጉበት ተመለሱ፤ ከብዙ ዘመን ጀምሮ ሰፊ አውራጃቸውን ይዘውባቸው ነበርና የቀሩትን በተራራማው ሀገርና በሜዳው የነበሩትን መንደሮችና ከተሞች ወሰዱ። እስራኤላውያን የድል በዓል ማክበራቸው 8 ታላቁ ካህን ኢዮአቄምና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የእስራኤል ልጆች ሽማግሌዎችም እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን በጎ ነገር ያዩ ዘንድ፥ ዮዲትንም ያዩአት ዘንድ፥ ከእርሷም ጋራ ሰላምታ ያደርጉ ዘንድ መጡ። 9 ወደ እርሷም በገቡ ጊዜ ሁሉም በአንድነት መረቋት፤ እንዲህም አሏት፥ “የኢየሩሳሌም ልዕልና አንቺ ነሽ፤ የእስራኤልም ክብራቸው አንቺ ነሽ፤ የወገኖቻችንም መመኪያ አንቺ ነሽ፤ 10 ይህ ሁሉ በእጅሽ ተደርጓልና፥ ይህንም በጎ ነገር ለእስራኤል አድርገሻልና፥ እግዚአብሔርም እነርሱን ወዷልና፥ ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ለዘለዓለሙ ይባርክሽ!” ሕዝቡም ሁሉ፥ “አሜን” አሉ። 11 ሕዝቡም ሠላሳ ቀን ሰፈራቸውን በረበሩ፤ ለዮዲትም የሆሎፎርኒስን ድንኳንና የብሩን ዕቃ ሁሉ፥ ዙፋኑንና ያለውንም ገንዘብ ሁሉ ሰጧት፤ እርሷም ወስዳ በበቅሎዋ ጫነች፤ ሠረገላዎችዋንም ነድታ ከእርሷ ጋር ይዛ ገባች። 12 የእስራኤልም ሴቶች ሁሉ ያይዋት ዘንድ፥ ይመርቋትም ዘንድ ወደ እርሷ ሮጠው ተሰበሰቡ፤ ታላቅ በዓልንም አደረጉላት፤ ዘንባባውንም በእጅዋ ያዘች፤ ከእርሷ ጋራ ላሉ ሴቶችም ሰጠች። 13 ለእርስዋና ከእርስዋ ጋር ለነበረችውም ብላቴና የወይራ ጕንጕን አደረጉላቸው፤ በሕዝቡም ፊት ሴቶችን ሁሉ እየመራች በዝማሬ ሄደች፤ የእስራኤልም አርበኞች ሁሉ የጦር መሣሪያቸውን ከዘንባባ ጋር ይዘው እየዘመሩ ተከተሏት። |