本书并非出自上帝启示,且不属于基督教正典或犹太教塔纳赫的一部分。仅为历史与研究目的而展示。 查看完整说明 መጽሐፈ ዮዲት 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የዮዲት ምክር 1 ዮዲትም፥ “ወንድሞች፥ ስሙኝ፤ ይህን ቸብቸቦ ይዛችሁ በግንቡ ጫፍ ላይ ስቀሉት። 2 ከዚህ በኋላ ሲነጋ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ሁላችሁም የጦር መሣሪያችሁን ያዙ፤ አርበኞች የሆኑ ሰዎች ሁሉ ከከተማ ወደ ውጭ ይውጡ፤ የአሦራውያን ሠራዊት ጠባቂዎችም ወዳሉበት ቦታ እንደምትወርዱ ሆናችሁ አለቃ ለራሳችሁ ሹሙ። ነገር ግን አትውረዱ። 3 ሁላችሁም የጦር መሣሪያችሁን ያዙ፥ ዘበኞችም ባዩአችሁ ጊዜ የአሦር ሠራዊት አለቆችን ይቀሰቅሱ ዘንድ ወደ ሰፈራቸው ይሄዳሉ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሆሎፎርኒስ ድንኳን ይሮጣሉ፤ አያገኙትም፤ ከዚያም በኋላ እጅግ ፈርተው ከፊታችሁ ይሸሻሉ። 4 ከዚህ በኋላም እናንተና በእስራኤል አውራጃ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ተከተሏቸው፤ በጎዳናቸውም ሁሉ ርገጡአቸው። 5 ይህንም ከማድረጋችሁ በፊት የእስራኤልን ወገን የካደውን ከእኛም ጋር ይሞት ዘንድ እርሱን ወደ እኛ የላከውን እርሱ መሆኑን አይቶ ያውቅ ዘንድ አሞናዊውን አክዮርን ጥሩልኝ” አለቻቸው። 6 አክዮርንም ከዖዝያን ቤት ጠሩት፤ መጥቶም የሆሎፎርኒስን ራስ በአንድ ሰው እጅ ባየ ጊዜ ሰውነቱ ደንግጦ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል በግንባሩ ወደቀ። 7 በአነሡትም ጊዜ በዮዲት እግር ላይ ወደቀ፤ ሰገደላትም፤ “ከይሁዳ ቤትና ከሕዝቡ ሁሉ አንቺ የተባረክሽ ነሽ፤ ስምሽንም ሰምተው ይደነግጣሉ። 8 አሁንም በእነዚህ ወራት ያደረግሺውን ንገሪኝ” አላት። ዮዲትም ከወጣች ጀምሮ እስክትመለስ ድረስ ያደረገችውን ሁሉ በሕዝቡ መካከል ነገረችው። 9 ነገሯን ተናግራ በጨረሰች ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቃላቸውን አሰምተው ደነፉ፤ በየከተማቸውም በደስታ ቃል ጮኹ። 10 አክዮርም እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን ተአምራት በአየ ጊዜ ፈጽሞ በእግዚአብሔር አምኖ ተገዘረ። እስከ ዛሬም ድረስ ከቤተ እስራኤል ጋር አንድ ሆነ። የሆሎፎርኒስ ሞት እንደ ተገለጠ 11 በነጋም ጊዜ የሆሎፎርኒስን ቸብቸቦ በግንቡ ላይ ሰቀሉት፤ ወንዶቹም ሁሉ መሣሪያቸውን ይዘው ወጡ፤ በተራራውም ዐቀበት በኩል ከበቧቸው። 12 የአሦር ሠራዊትም በአዩአቸው ጊዜ ወደ ሹሞቻቸው ላኩ፤ እነርሱም ወደ አለቆቻቸው፥ ወደ ሹሞቻቸውና ገዢዎቻቸው ሄዱ። 13 ወደ ሆሎፎርኒስም ድንኳን መጥተው ለመጋቢው፥ “እነዚህ ባሮች እስከ መጨረሻው ይጠፉ ዘንድ ሊዋጉን ተደፋፍረው ወርደዋልና ጌታችንን ከእንቅልፉ ቀስቅሰው” አሉት። 14 ባግዋም ከዮዲት ጋር የተኛ መስሎታልና ገብቶ በድንኳኑ አንጻር ያለ በሩን መታ። 15 ቃል የሚመልስለት ሰውም በአጣ ጊዜ ድንኳኑን ተርትሮ ወደ እልፍኙ ገባ፤ ሬሳውንም በወለሉ ላይ ወድቆ አገኘው። ራሱም በላዩ አልነበረም። 16 እያለቀሰና እያቃሰተ በታላቅ ቃል ፈጽሞ ጮኸ፤ ልብሱንም ቀደደ። 17 ዮዲትም ወደምታድርበት ድንኳን ገባ፤ ነገር ግን አላገኛትም፤ ወደ ሕዝቡም እየሮጠ ሄዶ ጮኸላቸው። እንዲህም አላቸው፦ 18 “እነዚህ ባሮች አታለሉን፤ እነሆ፥ የሆሎፎርኒስ ሬሳው በምድር ላይ ወድቋልና፥ ራሱም በላዩ የለምና አንዲት ዕብራዊት ሴት በንጉሡ በናቡከደነፆር ቤት ላይ ኀፍረትን አድርጋለች።” 19 የአሦር የሠራዊት አለቆችም ይህን ነገር በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደዱ፤ ሰውነታቸውም ፈጽማ ደነገጠች፤ በታላቅ ድምፅም በሰፈር መካከል ፈጽመው ጮኹ። |