መሳፍንት 21 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ብንያማውያን ሚስቶችን እንዲያገኙ የተደረገ ምክር 1 የእስራኤልም ሰዎች፥ “ከእኛ ማንም ሰው ሴት ልጁን ለብንያም ልጆች በጋብቻ አይስጥ” ብለው በመሴፋ ተማማሉ። 2 ሕዝቡም ወደ ቤቴል መጥተው በዚያ በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ ተቀመጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጽኑዕ ልቅሶ አለቀሱ። 3 እነርሱም፥ “አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ መታጣቱ፥ ስለምን ይህ በእስራኤል ላይ ሆነ?” አሉ። 4 በነጋውም ሕዝቡ ማልደው ተነሡ፤ በዚያም መሠዊያ ሠሩ፤ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕትንም አቀረቡ። 5 የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ወደ መሴፋ ስላልወጣ ሰው፥ “እርሱ ፈጽሞ ይገደል” ብለው ታላቅ መሐላ ምለው ነበርና፥ “ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ ጉባኤ ወደ እግዚአብሔር ያልወጣ ማን ነው?” አሉ። 6 የእስራኤልም ልጆች ስለ ወንድማቸው ስለ ብንያም ልጆች አዝነው እንዲህ አሉ፥ “ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ ጠፍቶአል። 7 እኛ ልጆቻችንን እንዳንድርላቸው በእግዚአብሔር ምለናልና የተረፉት ሚስቶችን እንዲያገኙ ምን እንድርግ?” 8 እነርሱም፥ “ከእስራኤል ነገድ ወደ እግዚአብሔር ወደ መሴፋ ያልወጣ ማን ነው?” አሉ። እነሆም፥ ከኢያቢስ ገለዓድ ወደ ሰፈሩ ወደ ጉባኤው ማንም አልወጣም ነበር። 9 ሕዝቡም በተቈጠሩ ጊዜ፥ እነሆ፥ ከኢያቢስ ገለዓድ ነዋሪዎች ሰው አልተገኘም። 10 ማኅበሩም ወደዚያ ዐሥራ ሁለት ሺህ ኀያላን ሰዎችን ልከው፥ “ሂዱ በኢያቢስ ገለዓድም ያሉትን ሰዎች ሴቶችንም ሕዝቡንም በሰይፍ ስለት ግደሉ። 11 የምታደርጉትም ይህ ነው፤ ወንዱን ሁሉ፥ ወንድ የሚያውቁትንም ሴቶች ሁሉ ፈጽማችሁ አጥፉ፤ ደናግሉን ግን አትግደሉአቸው፤” ብለው አዘዙአቸው፤ እንዲሁም አደረጉ። 12 በኢያቢስ ገለዓድ በሚኖሩ መካከልም ወንድ ያላወቁ አራት መቶ ቆነጃጅት ደናግልን አገኙ፤ በከነዓንም ሀገር ወዳለችው ወደ ሴሎ ወደ ሰፈሩ አመጡአቸው። 13 ማኅበሩም ሁሉ በሬሞን ዐለት ወዳሉት ወደ ብንያም ልጆች መልእክተኞችን ላኩ፤ በሰላምም ጠሩአቸው። 14 በዚያም ጊዜ የብንያም ልጆች ወደ እስራኤል ልጆች ተመለሱ፤ የእስራኤልም ልጆች ከኢያቢስ ገለዓድ ሴቶች ያዳኑአቸውን ሴቶች ሰጡአቸው። በዚህም ተስማሙ። 15 እግዚአብሔርም በእስራኤል ነገድ ውስጥ ስብራት ስላደረገ ሕዝቡ ስለ ብንያም አዘኑ። 16 የማኅበሩ ሽማግሌዎችም፥ “ከብንያም ሴቶች ጠፍተዋልና የቀሩት ስዎች ሚስት እንዲያገኙ ምን እናደርጋለን?” አሉ። 17 ደግሞም፥ “ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዳይደመሰስ ከብንያም ላመለጡት ርስት ይኑር። 18 የእስራኤልም ልጆች፥ “ልጁን ለብንያም የሚሰጥ ርጉም ይሁን ብለው ምለዋልና እኛ ከልጆቻችን ሚስቶችን ለእነርሱ መስጠት አንችልም” አሉ። 19 እነርሱም፥ “እነሆ፥ በቤቴል በመስዕ በኩል፥ ከቤቴልም ወደ ሰቂማ በሚወስደው መንገድ በምሥራቅ በኩል በሌብና በዐዜብ በኩል ባለችው በሴሎ የእግዚአብሔር በዓል በየዓመቱ አለ” አሉ። 20 የብንያምንም ልጆች እንዲህ ብለው አዘዙአቸው፥ “ሂዱ በወይኑም ስፍራ ተደበቁ፤ 21 ተመልከቱም፤ እነሆ፥ የሴሎ ሴቶች ልጆች አታሞ ይዘው ለዘፈን ሲወጡ ከወይኑ ስፍራ ውጡ፤ ከሴሎ ሴቶች ልጆችም ለየራሳችሁ ሚስትን ንጠቁ፤ ወደ ብንያም ምድርም ሂዱ። 22 አባቶቻቸውና ወንድሞቻቸውም ሊጣሉአችሁ ወደ እኛ በመጡ ጊዜ፦ ስለ እኛ ማሩአቸው፥ እኛ ሚስት ለያንዳንዳቸው በሰልፍ አልወሰድንላቸውምና፥ እናንተም በደል ይሆንባችሁ ስለ ነበር አላጋባችኋቸውምና፥” እንላቸዋለን። 23 የብንያምም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ በቍጥራቸውም መጠን ከተነጠቁት ዘፋኞች ሚስትን ወሰዱ፤ ወደ ርስታቸውም ተመልሰው ሄዱ፤ ከተሞችንም ሠርተው ተቀመጡባቸው። 24 በዚያ ጊዜም የእስራኤል ልጆች ከዚያ ተነሡ፤ እያንዳንዱም ወደ ወገኑና ወደ ነገዱ ሄደ፤ ሰውም ሁሉ ከዚያ ወደ ርስቱ ተመለሰ። 25 በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር። |