መሳፍንት 20 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እስራኤል ከብንያም ልጆች ጋር እንደ ተዋጉ 1 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወጡ፤ ማኅበሩም ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ድረስ፥ ከገለዓድም ሰዎች ጋር፥ ወደ እግዚአብሔር ወደ መሴፋ እንደ አንድ ሰው ሆነው ተሰበሰቡ። 2 ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ የሕዝቡ ሁሉ አለቆች ሰይፍ በሚመዝዙ፥ በቍጥርም አራት መቶ ሺህ እግረኞች በሆኑ በእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። 3 የብንያምም ልጆች የእስራኤል ልጆች ወደ መሴፋ እንደ ወጡ ሰሙ። የእስራኤልም ልጆች፥ “ይህ ክፉ ነገር እንደምን እንደ ተደረገ ንገሩን” አሉ። 4 የተገደለችውም ሴት ባል ሌዋዊዉ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፥ “እኔና ዕቅብቴ በዚያ ለማደር ወደ ብንያም ሀገር ወደ ገባዖን መጣን። 5 የገባዖንም ሰዎች ተነሡብን፤ ቤቱንም በሌሊት በእኛ ላይ ከበቡት፤ ሊገድሉኝም ወደዱ፤ ዕቅብቴንም አዋረድዋት፤ አመነዘሩባትም፤ እርስዋም ሞተች። 6 እኔም ዕቅብቴን ይዤ በመለያያዋ ቈራረጥኋት፤ በእስራኤልም ዘንድ እንደዚህ ያለ ስንፍና ስለ ሠሩ ወደ እስራኤል ርስት አውራጃ ሁሉ ሰደድሁ። 7 እነሆ፥ የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ ሁላችሁ፥ ምክራችሁንና እዝናታችሁን በዚህ ስጡ።” 8 ሕዝቡም ሁሉ እንደ አንድ ሰው ተነሥተው እንዲህ አሉ፥ “ከእኛ ዘንድ ማንም ወደ ሀገሩ አይሄድም፤ ወደ ቤቱም አይመለስም። 9 አሁንም በገባዖን ላይ እንዲህ አድርጉ፤ በየዕጣችን እንዘምትባቸዋለን። 10 በእስራኤል ላይ ስላደረጉት ስንፍና ሁሉ የብንያም ገባዖንን ይወጉ ዘንድ ለሚሄዱ ሕዝብ በመንገድ ስንቅ የሚይዙ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከመቶው ዐሥር ሰው፥ ከሺሁም መቶ ሰው፥ ከዐሥሩም ሺህ አንድ ሺህ ሰው እንወስዳለን።” 11 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ እንደ አንድ ሰው ሆነው በከተማዪቱ ላይ ተሰበሰቡ። 12 የእስራኤልም ነገዶች፥ “በእናንተ መካከል የተደረገ ይህ ክፉ ነገር ምንድን ነው?” ብለው ወደ ብንያም ነገድ ሁሉ ሰዎችን ላኩ። 13 “አሁንም በገባዖን ውስጥ የበደሉ የዐመፅ ሰዎችን እንድንገድላቸው አውጥታችሁ ስጡን፤ ከእስራኤልም ልጆች ክፋትን እናርቃለን።” የብንያም ልጆች ግን የወንድሞቻቸውን የእስራኤልን ልጆች ቃል ሊሰሙ አልወደዱም። 14 የብንያምም ልጆች ከእስራኤል ልጆች ጋር ሊዋጉ ከየከተማዎቻቸው ወደ ገባዖን ተሰበሰቡ። 15 በዚያም ቀን ከየከተማው የመጡ የብንያም ልጆች ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸውም ከገባዖን ሰዎች ሌላ ሃያ አምስት ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ነበሩ፤ ከገባዖንም ሰባት መቶ የተመረጡ ሰዎች ተቈጠሩ፤ 16 ከእነዚያም ሕዝብ ሁሉ ሰባት መቶ የተመረጡ፥ ሁለቱም እጆቻቸው ቀኝ የሆኑላቸው ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህም ሁሉ ድንጋይ ይወነጭፉ ነበር፤ አንዲት ጠጕርስ እንኳ አይስቱም ነበር። 17 ከብንያምም ልጆች ሌላ የእስራኤል ሰዎች አራት መቶ ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ተቈጠሩ፤ እነዚህም ሁሉ ሰልፈኞች ነበሩ። 18 የእስራኤልም ልጆች ተነሥተው ወደ ቤቴል ወጡ፤ እግዚአብሔርንም፥ “የብንያምን ልጆች ለመውጋት መሪ ሆኖ ማን ይውጣልን?” ብለው ጠየቁት፤ እግዚአብሔርም፥ “ይሁዳ መሪ ይሁን” አለ፤ 19 የእስራኤልም ልጆች በማለዳ ተነሥተው በገባዖን ፊት ሰፈሩ። 20 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከብንያም ጋር ሊዋጉ ወጡ፤ በገባዖንም ገጠሙአቸው። 21 የብንያምም ልጆች ከገባዖን ወጡ፤ በዚያም ቀን ከእስራኤላውያን ሃያ ሁለት ሺህ ሰዎችን በምድር ላይ ገደሉ። 22 የእስራኤልም ሰዎች ተበራቱ፤ በፊተኛውም ቀን በተሰለፉበት ስፍራ ደግመው ተሰለፉ። 23 የእስራኤልም ልጆች ወጥተው በእግዚአብሔር ፊት እስከ ማታ ድረስ አለቀሱ፤ እግዚአብሔርንም፥ “ከወንድሞቻችን ከብንያም ልጆች ጋር ለመዋጋት ዳግመኛ እንቀርባለን?” ብለው ጠየቁ። እግዚአብሔርም “በእነርሱ ላይ ውጡ” አለ። 24 በሁለተኛውም ቀን የእስራኤል ልጆች ከብንያም ልጆች ጋር ሊዋጉ ቀረቡ። 25 በሁለተኛውም ቀን የብንያም ልጆች ሊገጥሙአቸው ከገባዖን ወጡ፤ ከእስራኤልም ልጆች ደግሞ ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰዎችን በምድር ላይ ገደሉ፤ እነዚህም ሁሉ ሰይፍ የሚመዝዙ ነበሩ። 26 የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሕዝቡም ሁሉ ወጥተው ወደ ቤቴል መጡ፤ አለቀሱም፤ በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ በዚያም ቀን እስከ ማታ ድረስ ጾሙ፤ በእግዚአብሔርም ፊት የሚቃጠል መሥዋዕትንና የደኅንነት መሥዋዕትን አቀረቡ። 27 በዚያም ዘመን የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በዚያ ነበረችና፥ የእስራኤል ልጆች እግዚአብሔርን ጠየቁ፤ 28 በዚያም ዘመን የአሮን ልጅ የአልዓዛር ልጅ ፊንሐስ በፊቷ ይቆም ነበርና። “ከወንድሞቻችን ከብንያም ልጆች ጋር ለመዋጋት ዳግመኛ እንውጣን? ወይስ እንቅር?” አሉ። እግዚአብሔርም፥ “ነገ በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጡ” አላቸው። 29 የእስራኤልም ልጆች ገባዖንን የሚከብቡአት ሰዎችን በዙሪያዋ አኖሩባት። 30 በሦስተኛውም ቀን የእስራኤል ልጆች ወደ ብንያም ልጆች ወጡ፤ በገባዖንም ፊት እንደ ቀድሞው ጊዜ ተዋጉአቸው። 31 የብንያምም ልጆች በሕዝቡ ላይ ወጡ፤ ከከተማዪቱም ሸሹ፤ እንደ ቀድሞውም ጊዜ፥ በአውራዎቹ መንገዶች፥ አንደኛው ወደ ቤቴል፥ ሁለተኛውም ወደ ገባዖን ሜዳ በሚወስዱት መንገዶች ላይ ሕዝቡን ይመቱ፥ ይገድሉም ጀመር፤ ከእስራኤልም ሠላሳ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ። 32 የብንያምም ልጆች፥ “እንደ ቀድሞው በፊታችን ይሞታሉ” አሉ። የእስራኤል ልጆች ግን፥ “እንሽሽ፤ ከከተማም ወደ መንገድ እናርቃቸው” አሉ። 33 የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከስፍራቸው ተነሥተው በበዓልታምር ተዋጉ። ከእስራኤልም አድፍጠው የነበሩት ከስፍራቸው ከገባዖን ምዕራብ ወጡ። 34 ከእስራኤልም ሁሉ የተመረጡ ዐሥር ሺህ ሰዎች ወደ ገባዖን አንጻር መጡ፤ ውጊያውም በርትቶ ነበር፤ መከራም እንዲያገኛቸው አላወቁም ነበር። 35 እግዚአብሔርም ብንያምን በእስራኤል ፊት ጣላቸው፤ በዚያም ቀን የእስራኤል ልጆች ከብንያም ሃያ አምስት ሺህ አንድ መቶ ሰዎችን ገደሉ፤ እነዚህም ሁሉ ሰይፍ የሚመዝዙ ነበሩ። እስራኤል የብንያምን ልጆች ድል እንዳደረጉ 36 የብንያም ልጆችም እንደ ተመቱ አዩ፤ የእስራኤል ልጆች ግን በገባዖን ላይ ባኖሩት ድብቅ ጦር ታምነዋልና ለብንያም ስፍራ ለቀቁላቸው። 37 ተደብቀው የነበሩትም ፈጥነው ወደ ገባዖን ሮጡ፤ ተደብቀው የነበሩትም መጥተው ከተማውን ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ። 38 የተደበቁትም ሰዎች ከከተማው ብዙ ጢስ እንደ ደመና እንዲያስነሡ በእስራኤል ልጆችና በተደበቁት ሰዎች መካከል ምልክት ተደርጎ ነበር። 39 የእስራኤልም አርበኞች ከሰልፉ ተመለሱ፤ ብንያማውያንም እንደ ቀድሞው ሰልፍ በፊታችን ተመትተዋል እያሉ ከእስራኤል ሰዎች ሠላሳ የሚያህሉ ሰዎችን መምታትና መግደል ጀመሩ። 40 ምልክቱም በጢሱ ዐምድ ከከተማው ሊወጣ በጀመረ ጊዜ ብንያማውያን ወደኋላቸው ተመለከቱ፤ እነሆም፥ የሞላ ከተማው ጥፋት ወደ ሰማይ ወጣ። 41 የእስራኤልም ልጆች ተመለሱ፤ የብንያምም ሰዎች ተሸበሩ፤ ክፉ ነገር እንደ ደረሰባቸውም አዩ። 42 ከእስራኤልም ሰዎች ፊት ወደ ምድረ በዳ መንገድ ሸሹ፤ ሰልፉም ደረሰባቸው፤ ከየከተማውም የወጡት በመካከላቸው ገደሉአቸው። 43 ብንያማውያንንም ወግተው አጠፉአቸው፤ በምሥራቅ በኩል ባለው በገባዖንም ፈጽመው ደመሰሱአቸው። 44 ከብንያምም ዐሥራ ስምንት ሺህ ሰው ሞተ፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ሰዎች ነበሩ። 45 ከእነርሱም የተረፉት ተመልሰው ወደ ምድረ በዳ ወደ ሬሞን ዓለት ሸሹ፤ ከእነርሱም በየመንገዱ ላይ አምስት ሺህ ሰውን ለቀሙ፤ ወደ ጊድዓምም አሳደዱአቸው፤ ከእነርሱም ሁለት ሺህ ሰዎችን ገደሉ። 46 እንዲሁም በዚያ ቀን ከብንያም የሞቱት ሃያ አምስት ሺህ ሰይፍ የሚመዝዙ ሰዎች ነበሩ፤ እነዚህ ሁሉ ጽኑዓን ሰዎች ነበሩ። 47 ስድስቱም መቶ ሰዎች ተመልሰው ወደ ምድረ በዳ ወደ ሬሞን ዓለት ሸሹ፤ በሬሞንም ዓለት አራት ወር ተቀመጡ። 48 የእስራኤልም ሰዎች በብንያም ልጆች ላይ ዳግመኛ ተመለሱ፤ ሞላውን ከተማ፥ ከብቱንም፥ ያገኙትንም ሁሉ በሰይፍ ስለት አጠፉ፤ ያገኙትንም ከተማ ሁሉ በእሳት አቃጠሉ። |