መሳፍንት 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)አንድ ሌዋዊና ዕቅብቱ 1 በዚያም ዘመን ለእስራኤል ንጉሥ አልነበራቸውም። በተራራማውም በኤፍሬም ሀገር ማዶ የተቀመጠ አንድ ሌዋዊ ሰው ነበረ፤ ከይሁዳ ቤተ ልሔምም ዕቅብት አገባ። 2 ዕቅብቱም ተጣላችው፤ ትታውም ወደ አባቷ ቤት ወደ ይሁዳ ቤተ ልሔም ሄደች፤ በዚያም አራት ወር ተቀመጠች። 3 ባልዋም ተነሣ፤ ከእርስዋም ዕርቅ ሽቶ ወደ እርሱ ሊመልሳት ፍለጋዋን ተከትሎ ሄደ፤ ከእርሱም ጋር አንድ ብላቴና፥ ሁለትም አህዮች ነበሩ። እርሱም ወደ አባቷ ቤት ሄደ፤ የብላቴናዪቱም አባት ባየው ጊዜ ደስ ብሎት ተቀበለው። 4 የብላቴናዪቱም አባት አማቱ ወደ ቤቱ አገባው፤ በቤቱም ሦስት ቀን ተቀመጠ፤ በሉም፤ ጠጡም፤ በዚያም አደሩ። 5 በአራተኛውም ቀን ማልደው ተነሡ፤ እርሱም ለመሄድ ተነሣ፤ የብላቴናዪቱም አባት አማቹን፥ “ሰውነትህን በቁራሽ እንጀራ አበርታ፤ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ” አለው። 6 ሁለቱም በአንድ ላይ ተቀመጡ፤ በሉም፤ ጠጡም፤ የብላቴናዪቱም አባት ሰውዬውን፥ “ዛሬ ደግሞ ከዚህ እደር ልብህንም ደስ ይበለው” አለው። 7 ሰውዬውም ሊሄድ ተነሣ፤ አማቱ ግን ግድ አለው፤ ዳግመኛም በዚያ አደረ። 8 በአምስተኛውም ቀን ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤ የብላቴናዪቱም አባት፥ “እህል ብላ፤ ከዚህም በኋላ ፀሐይ ሲበርድ ትሄዳለህ” አለው። ሁለቱም በሉ፤ ጠጡም። 9 ሰውዬውም ከዕቅብቱና ከብላቴናው ጋር ለመሄድ ተነሣ፤ የብላቴናዪቱ አባት አማቱም፥ “እነሆ፥ መሽትዋል፤ ፀሐዩም ሊጠልቅ ደርሷል፤ ዛሬም እዚህ እደር፤ በዚህም ተቀመጥ፤ ልብህም ደስ ይበለው፤ በጥዋትም መንገዳችሁን ትገሠግሣላችሁ፤ ወደ ቤትህም ትገባለህ” አለው። 10 ሰውዬው ግን በዚያ ሌሊት ለማደር አልፈቀደም፤ ተነሥቶም ሄደ፤ ኢየሩሳሌምም ወደ ተባለችው ወደ ኢያቡስ ፊት ለፊት ደረሰ። ከእርሱም ጋር ሁለት የተጫኑ አህዮች ነበሩ፤ ዕቅብቱም ከእርሱ ጋር ነበረች። 11 በኢያቡስም አንጻር ገና ሳሉ ፀሐይዋ ተቈለቈለች፤ ብላቴናውም ጌታውን፥ “ና፤ ወደዚህች ወደ ኢያቡሳውያን ከተማ፥ እባክህ እናቅና፤ በእርስዋም እንደር” አለው። 12 ጌታውም፥ “ከእስራኤል ልጆች ወዳልሆነች ወደ እንግዳ ከተማ አንገባም፤ እኛ ወደ ገባዖን እንለፍ” አለው። 13 ብላቴናውንም፥ “ና፤ ከእነዚህ ስፍራ ወደ አንዱ እንቅረብ፤ በገባዖን ወይም በራማ እንደር” አለው። 14 አልፈውም ሄዱ፤ የብንያምም ነገድ በምትሆነው በገባዖን አጠገብ ሳሉ ፀሐይ ገባችባቸው። 15 በገባዖንም ገብተው ያድሩ ዘንድ ወደዚያ አቀኑ። ገብተውም በከተማው አደባባይ በተቀመጡ ጊዜ ወደ ቤቱ የሚያስገባቸውና የሚያሳድራቸው አልነበረም። 16 እነሆም አንድ ሽማግሌ ከእርሻው ሥራ ወደ ማታ መጣ፤ ይህም ሰው ከተራራማው ከኤፍሬም ሀገር ነበረ፤ በገባዖንም በእንግድነት ተቀምጦ ነበር፤ የዚያ ሀገር ሰዎች ግን የብንያም ልጆች ነበሩ። 17 ዐይኑንም አንሥቶ መንገደኛውን በከተማው አደባባይ አየ፤ ሽማግሌውም፥ “ወዴት ትሄዳለህ? ከወዴትስ መጣህ?” አለው። 18 እርሱም፥ “እኛ ከይሁዳ ቤተ ልሔም ወደ ተራራማው ወደ ኤፍሬም ሀገር ማዶ እናልፋለን፤ እኔ ከዚያ ነኝ፤ ወደ ይሁዳ ቤተ ልሔምም ሄጄ ነበር፥ አሁንም ወደ ቤቴ እሄዳለሁ፤ በቤቱም የሚያሳድረኝ አጣሁ፤ 19 ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ ለእኔና ለገረድህ ከባሪያዎችህም ጋር ላለው ብላቴና እንጀራና የወይን ጠጅ አለን፤ ከሚያስፈልገን ሁሉ አንዳችም አላጣንም” አለው። 20 ሽማግሌውም ሰው፥ “ሰላም ከአንተ ጋር ይሁን፤ የምትሻውንም ሁሉ እኔ እሰጥሃለሁ፤ በአደባባይ ግን አትደር” አለው። 21 ወደ ቤቱም አስገባው፤ ለአህዮቹም ገፈራ ጣለላቸው፤ እግራቸውንም ታጠቡ፤ በሉም፤ ጠጡም። የኢያቡሴዎን ሰዎች በደል 22 ሰውነታቸውንም ደስ ባሰኙ ጊዜ የኃጥኣን ልጆች የሆኑ የከተማው ሰዎች ቤቱን ከበቡ፤ በሩንም ይደበድቡ ነበር፤ ባለቤቱንም ሽማግሌውን ሰው፥ “ወደ ቤትህ የገባውን ሰው እንድንደርስበት አውጣልን” አሉት። 23 ባለቤቱም ሽማግሌው ወደ እነርሱ ወጥቶ፥ “ወንድሞቼ ሆይ! ይህን ክፉ ነገር ታደርጉ ዘንድ አይገባችሁም፤ ይህ ሰው ወደ ቤቴ ከገባ በኋላ እንደዚህ ያለ ስንፍና አትሥሩ። 24 ድንግል ልጄና የእርሱም ዕቅብት እነሆ፥ አሉ፤ አሁንም አወጣቸዋለሁ፤ አዋርዱአቸው፤ በዐይናችሁም ፊት ደስ የሚላችሁን አድርጉባቸው፤ ነገር ግን በዚህ ሰው ላይ እንደዚህ ያለ የስንፍና ሥራ አታድርጉ” አላቸው። 25 ሰዎቹ ግን ሊሰሙት አልፈቀዱም፤ ሰውየውም ዕቅብቱን ይዞ ወደ እነርሱ አወጣላቸው፤ አዋረድዋትም፤ ሌሊቱንም ሁሉ እስኪነጋ ድረስ አመነዘሩባት፤ ጎህም በቀደደ ጊዜ ለቀቁአት። 26 ሴቲቱም ማለዳ መጣች፤ ጌታዋም ባለበት በሰውዬው ቤት ደጅ ወድቃ እስኪነጋ ድረስ በዚያ ቀረች። 27 ጌታዋም ማለዳ ተነሣ፤ የቤቱንም ደጅ ከፈተ፤ መንገዱንም ለመሄድ ወጣ፤ እነሆም፥ ዕቅብቱ ሴት በቤቱ ደጃፍ ላይ ወድቃ፥ እጆችዋም በመድረኩ ላይ ወድቀው አገኛት። 28 እርሱም፥ “ተነሺ እንሂድ” አላት፤ እርስዋ ግን ሞታ ነበርና አልመለሰችም፤ በዚያ ጊዜም በአህያው ላይ ጫናት፤ ተነሥቶም ወደ ስፍራው ተመለሰ። 29 ወደ ቤቱም በገባ ጊዜ ካራ አነሣ፤ ዕቅብቱንም ይዞ ከአጥንቶችዋ መለያያ ላይ ለዐሥራ ሁለት ቈራርጦ ወደ እስራኤል ሀገር ሁሉ ሰደደ። 30 ከዚያም በኋላ ያያት ሁሉ እንዲህ አለ፥ “እስራኤል ከግብፅ ከወጡ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ያለ ነገር የሆነበት ጊዜ የለም፤ የታየበትም ጊዜ የለም፤” ያም ሰው እነዚያን የላካቸውን ሰዎች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፥ “የእስራኤልን ሰዎች እንዲህ በሏቸው፦ እስራኤል ከግብፅ ከወጡ ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ እንዲህ የሆነበት ጊዜ አለን? እናንተ ተመካከሩበት፤ የሚበጀውንም ተነጋገሩ።” |