መሳፍንት 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ከጊዜም በኋላ በስንዴ መከር ጊዜ ሶምሶን የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ሊጠይቅ ሄደና፥ “ወደ ጫጕላ ቤት ወደ ሚስቴ ልግባ” አለ፤ አባቷ ግን እንዳይገባ ከለከለው። 2 አባቷም፥ “ፈጽመህ ጠላህዋት ያልህ መስሎኝ ለሚዜህ አጋባኋት፤ ታናሽ እኅቷ ከእርስዋ ይልቅ የተዋበች አይደለችምን? እባክህ በእርስዋ ፋንታ አግባት” አለው። 3 ሶምሶንም፥ “ከእንግዲህ ወዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ ክፉ ባደርግ እኔ ንጹሕ ነኝ” አላቸው። 4 ሶምሶንም ሄዶ ሦስት መቶ ቀበሮችን ያዘ፤ ችቦም ወስዶ ሁለት ሁለቱን ቀበሮዎች በጅራታቸው አሰረ፤ በሁለቱም ጅራቶች መካከል አንድ ችቦ አደረገ። 5 ችቦውንም አንድዶ በቆመው በፍልስጥኤማውያን እህል መካከል ሰደዳቸው፤ ነዶውንም፥ ክምሩንም፥ የቆመዉንም እህል፥ ወይኑንም፥ ወይራዉንም አቃጠለ። 6 ፍልስጥኤማውያንም፥ “ይህን ያደረገ ማን ነው?” አሉ። እነርሱም፥ “ሚስቱን ወስዶ ለሚዜው አጋብቶበታልና የቴምናታዊዉ አማች ሶምሶን ነው” አሉአቸው። ፍልስጥኤማውያንም ወጥተው የአባቷን ቤትና እርስዋን አባቷንም በእሳት አቃጠሉ። 7 ሶምሶንም አላቸው- “ይህን ብታደርጉም ደስ አይለኝም፤ በቀሌ ከአንድ ሰው ብቻ አይደለም፤ ሁላችሁንም እበቀላችኋለሁ፤ ከዚያም በኋላ አርፋለሁ።” 8 ሶምሶንም ጭን ጭናቸውን ብሎ በታላቅ አገዳደል መታቸው፤ ወርዶም ኢጣም በምትባል ዋሻ በወንዝ ዳር ተቀመጠ። ሶምሶን ፍልስጥኤማውያንን ድል እንዳደረገ 9 ፍልስጥኤማውያንም ወጡ፤ በይሁዳም ሰፈሩ፤ የአህያ መንጋጋ አጥንት በተባለ ቦታም ተበታትነው ተቀመጡ። 10 የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ “በእኛ ላይ የወጣችሁት ለምንድን ነው?” አሉ። እነርሱም፥ “ሶምሶንን ልናስር፥ እንዳደረገብንም ልናደርግበት መጥተናል” አሏቸው። 11 ከይሁዳም ሰዎች ሦስት ሺህ የሚያህሉ በኢጣም ዓለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሶምሶንን፥ “ገዢዎቻችን ፍልስጥኤማውያን እንደሆኑ አታውቅምን? ያደረግህብን ይህ ምንድን ነው?” አሉት። ሶምሶንም፥ “እንዳደረጉባችሁ እንዲሁ አደረግሁባቸው” አላቸው። 12 እነርሱም፥ “አስረን በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፈን ልንሰጥህ መጥተናል” አሉት። ሶምሶንም፥ “እናንተ እንዳትገድሉኝ ማሉልኝ፤ ለእነርሱም አሳልፋችሁ ስጡኝ፤ እናንተ ግን ከእኔ ጋር አትዋጉ” አላቸው። 13 እነርሱም፥ “በገመድ አስረን በእጃቸው አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ አንገድልህም” ብለው ማሉለት። በሁለትም አዲስ ገመድ አስረው ከዓለቱ ውስጥ አወጡት። 14 የአህያ መንጋጋ አጥንት ወደ ተባለ ቦታም ደረሰ፤ ፍልስጥኤማውያንም ደንፍተው ተቀበሉት፤ ወደ እርሱም ሮጡ። የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ አደረ፤ በክንዱም ያሉ እነዚያ ገመዶች በእሳት ላይ እንደ ተጣለ ገለባ ሆኑ፤ ማሰሪያውም ከክንዱ ተፈታ፤ 15 የወደቀ የአህያ መንጋጋ አጥንትንም በመንገድ አገኘ። እጁንም ዘርግቶ ወሰደው፤ በእርሱም አንድ ሺህ ሰው ገደለ። 16 ሶምሶንም፥ “በአህያ መንጋጋ አጥንት ክምር በክምር ላይ አድርጌአቸዋለሁ፤ በአህያ መንጋጋ አጥንት አንድ ሺህ ሰው ገድያለሁና” አለ። 17 መናገሩንም በፈጸመ ጊዜ መንጋጋውን ከእጁ ጣለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም “ቀትለ አጽመ መንሰክ” ብሎ ጠራው። 18 እርሱም እጅግ ተጠምቶ ነበርና፥ “አንተ ይህችን ታላቅ ማዳን በባሪያህ እጅ ሰጥተሃል፤ አሁንም በጥም እሞታለሁ፤ ባልተገረዙትም እጅ እወድቃለሁ” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 19 እግዚአብሔርም የዚያችን የአህያ መንጋጋ አጥንት ስንጥቃት ከፈተ፤ ከእርስዋም ውኃ ወጣ፤ እርሱም ጠጣ፤ ነፍሱም ተመለሰች፤ ከውኃ ጥሙም ዐረፈ። ስለዚህም የዚያ ቦታ ስም እስከ ዛሬ ድረስ “ነቅዐ አጽመ መንሰክ” ተብሎ ተጠራ። 20 በፍልስጥኤማውያንም ዘመን እስራኤልን ሃያ ዓመት ገዛቸው። |