መሳፍንት 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሶምሶን ፍልስጥኤማዊትን ሴት እንዳገባ 1 ሶምሶንም ወደ ቴምናታ ወረደ፤ በቴምናታም ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አየ፤ እርስዋም በፊቱ ደስ አለችው። 2 ወጥቶም ለአባቱና ለእናቱ፥ “በቴምናታ ከፍልስጥኤማውያን ልጆች አንዲት ሴት አይቻለሁ፤ አሁንም እርስዋን አጋቡኝ” አላቸው። 3 አባቱና እናቱም፥ “ካልተገረዙት ከፍልስጥኤማውያን ሚስት ለማግባት ትሄድ ዘንድ ከወንድሞችህ ሴቶች ልጆች፥ ከሕዝቤም ሁሉ መካከል ሴት የለችምን?” አሉት። ሶምሶንም አባቱን፥ “ለዐይኔ እጅግ ደስ አሰኝታኛለችና እርስዋን አጋባኝ” አለው። 4 አባቱና እናቱም ነገሩ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ አላወቁም፤ እርሱ ከፍልስጥኤማውያን በቀልን ይመልስ ዘንድ ይፈልግ ነበርና። በዚያም ወራት ፍልስጥኤማውያን እስራኤልን ይገዙ ነበር። 5 ሶምሶንም፥ አባቱና እናቱም ወደ ቴምናታ ወረዱ፤ በቴምናታም ወዳለው ወደ ወይኑ ስፍራ ፈቀቅ አለ፤ እነሆም፥ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት። 6 የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ አደረ፤ የፍየል ጠቦትን እንደሚጥልም ጣለው፤ በእጁም እንደ ኢምንት ሆነ፤ ያደረገውንም ለአባቱና ለእናቱ አልተናገረም። 7 ሂደውም ከሴቲቱ ጋር ተነጋገሩ፤ ሶምሶንንም በፊቱ ደስ አሰኘችው። 8 ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ሊያገባት ተመለሰ፤ የአንበሳውንም ሬሳ ያይ ዘንድ ከመንገድ ፈቀቅ አለ፤ እነሆም፥ በአንበሳው አፍ ውስጥ ንብ ሰፍሮበት ነበር፤ ማርም ነበረበት። 9 ወስዶም በላ፤ እየበላም ሄደ፤ ወደ አባቱና ወደ እናቱም ደረሰ፤ ሰጣቸውም፤ እነርሱም በሉ፤ ማሩንም ከአንበሳው አፍ ውስጥ እንዳወጣው አልነገራቸውም። 10 አባቱም ወደ ሴቲቱ ወረደ፤ ጐበዞችም እንዲሁ ያደርጉ ነበርና ሶምሶን በዚያ ሰባት ቀን በዓል አደረገ። 11 ከዚህም በኋላ ፈርተው ሠላሳ ሰዎችን በእርሱ ላይ ሾሙ፤ ከእርሱም ጋር ተቀመጡ። 12 ሶምሶንም አላቸው፥ “እንቆቅልሽ ልስጣችሁ፤ በሰባቱም በበዓሉ ቀኖች ውስጥ ፈትታችሁ ብትነግሩኝ፥ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ እሰጣችኋለሁ፤ 13 መፍታት ባትችሉ ግን እናንተ ለእኔ ሠላሳ የበፍታ ቀሚስና ሠላሳ ልውጥ ልብስ ትሰጡኛላችሁ።” እነርሱም፥ “ምሳሌህን መስልና እንስማህ” አሉት። 14 እርሱም፥ “ከበላተኛ መብል ወጣ፤ ከብርቱም ጣፋጭ ወጣ” አላቸው። እስከ ሦስት ቀንም እንቆቅልሹን መፍታት አልቻሉም። 15 ከዚህ በኋላ በአራተኛው ቀን የሶምሶንን ሚስት፥ “እንቆቅልሹን እንዲነግርሽ ባልሽን አባብይው፤ አለዚያም አንቺንና የአባትሽን ቤት በእሳት እናቃጥላለን፤ ወይስ ወደዚህ የጠራችሁን ልታደኸዩን ነውን?” አሉአት። 16 የሶምሶንም ሚስት በፊቱ እያለቀሰችበት፥ “ጠልተኸኛል፤ ከቶም አትወድደኝም፤ ለሕዝቤ ልጆች የነገርኸውን እንቆቅልሽህን አልነገርኸኝምና” አለችው። እርሱም፥ “እነሆ፥ ለአባቴና ለእናቴ አልነገርኋቸውም፤ ለአንቺ እነግርሻለሁን?” አላት። 17 ሰባቱንም የበዓል ቀን አለቀሰችበት፤ እርስዋም ነዝንዛዋለችና በሰባተኛው ቀን ነገራት። ለሕዝብዋም ልጆች ነገረቻቸው። 18 በሰባተኛዪቱም ቀን ፀሐይ ሳትገባ የከተማዪቱ ሰዎች፥ “ከማር የሚጣፍጥ ምንድን ነው? ከአንበሳስ የሚበረታ ማን ነው?” አሉት። ሶምሶንም፥ “በጥጃዬ ባላረሳችሁ ኑሮ የእንቆቅልሼን ትርጓሜ ባላወቃችሁም ነበር” አላቸው። 19 የእግዚአብሔርም መንፈስ በላዩ ወረደ፤ ወደ አስቀሎናም ወረደ፤ ከዚያም ሠላሳ ሰዎችን ገደለ፤ ልብሳቸውንም ገፍፎ እንቆቅልሹን ለነገሩት ሰዎች ሰጠ። ሶምሶንም ተቈጣ፤ ወደ አባቱም ቤት ተመለሰ። 20 የሶምሶንም ሚስት ከስር ሚዜው ጋር ተቀመጠች። |