መሳፍንት 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሶምሶን ልደት 1 የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን እጅ አርባ ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው። 2 ከዳን ወገን የሆነ ማኑሄ የሚባል አንድ የሶራሕ ሰው ነበረ፤ ሚስቱም መካን ነበረች፤ ልጅም አልወለደችም ነበር። 3 የእግዚአብሔርም መልአክ ለሴቲቱ ተገልጦ እንዲህ አላት፥ “እነሆ፥ አንቺ መካን ነሽ፤ ልጅም አልወለድሽም፤ ነገር ግን ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ። 4 አሁንም ተጠንቀቂ፤ የወይን ጠጅንና የሚያሰክር መጠጥንም አትጠጪ፤ ርኩስም ነገር አትብዪ። 5 እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ልጁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና በራሱ ላይ ምላጭ አይድረስበት፤ እርሱም እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅ ማዳን ይጀምራል።” 6 ሴቲቱም ወደ ባልዋ መጥታ፥ “አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ እኔ መጣ፤ መልኩም እንደ እግዚአብሔር መልአክ እጅግ የሚያስደነግጥ ነበረ፤ ከወዴትም እንደ መጣ ጠየቅሁት፥ እርሱም ስሙን አልነገረኝም። 7 እርሱም፦ እነሆ፥ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ እንግዲህ የወይን ጠጅንና የሚያሰክር መጠጥን አትጠጪ፥ ርኩስ ነገርንም አትብዪ፤ ልጁ ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ እስኪሞት ድረስ ለእግዚአብሔር የተለየ ናዝራዊ ይሆናልና አለኝ” ብላ ተናገረች። 8 ማኑሄም፥ “ጌታ ሆይ፥ ወደ እኛ የላክኸው የእግዚአብሔር ሰው፥ እባክህ እንደገና ወደ እኛ ይምጣ፤ ለሚወለደውም ልጅ ምን እንደምናደርግ ያስገንዝበን” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ለመነ። 9 እግዚአብሔርም የማኑሄን ቃል ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ እንደ ገና በእርሻ ውስጥ ተቀምጣ ሳለች ወደ ሴቲቱ መጣ፤ ባልዋ ማኑሄ ግን ከእርስዋ ጋር አልነበረም። 10 ሴቲቱም ፈጥና ሮጠች ለባልዋም፥ “እነሆ፥ አስቀድሞ ወደ እኔ የመጣው ያ ሰው ደግሞ ተገለጠልኝ” ብላ ነገረችው። 11 ማኑሄም ተነሥቶ ሚስቱን ተከተለ፤ ወደ ሰውዬዉም መጥቶ፥ “ከሚስቴ ጋር የተነጋገርህ አንተ ነህን?” አለው። መልአኩም፥ “እኔ ነኝ” አለ። 12 ማኑሄም፥ “እነሆ፥ ቃልህ በደረሰ ጊዜ የልጁ ነገሩ፥ ግብሩስ ምንድን ነው?” አለው። 13 የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን፥ “ለሚስትህ ከነገርኋት ሁሉ ተጠበቁ። 14 ከወይንም ከሚወጣው ሁሉ አትብላ፤ የወይን ጠጅንና የሚያሰክር መጠጥንም አትጠጣ፤ ርኩስንም ነገር ሁሉ አትብላ፤ ያዘዝኋትን ሁሉ ጠብቁ” አለው። 15 ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ፥ “የፍየል ጠቦት እናዘጋጅልህ ዘንድ ግድ እንልሃለን” አለው። 16 የእግዚአብሔርም መልአክ ማኑሄን፥ “አንተ የግድ ብትለኝ እህልህን አልበላም፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ብታደርግ ለእግዚአብሔር አቅርበው” አለው። ማኑሄም የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን አላወቀም ነበር። 17 ማኑሄም የእግዚአብሔርን መልአክ፥ “ነገርህ በደረሰ ጊዜ እንድናከብርህ ስምህ ማን ነው” አለው። 18 የእግዚአብሔርም መልአክ፥ “ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ?” አለው። 19 ማኑሄም የፍየሉን ጠቦትና የእህሉን ቍርባን ወስዶ በድንጋይ ላይ ለእግዚአብሔር አቀረበው። መልአኩም ተአምራት አደረገ፤ ማኑሄና ሚስቱም ይመለከቱ ነበር። 20 ነበልባሉም ከመሠዊያዉ ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ በመሠዊያዉ ነበልባል ውስጥ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ማኑሄና ሚስቱም ተመለከቱ፤ በምድርም በግንባራቸው ወደቁ። 21 የእግዚአብሔርም መልአክ ዳግመኛ ለማኑሄና ለሚስቱ አልተገለጠም፤ ያን ጊዜም ማኑሄ የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ዐወቀ። 22 ማኑሄም ሚስቱን፥ “እግዚአብሔርን አይተናልና ሞትን እንሞታለን” አላት። 23 ሚስቱም፥ “እግዚአብሔርስ ሊገድለን ቢወድድ ኖሮ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን ከእጃችን ባልተቀበለን፥ ይህንም ነገር ሁሉ ባላሳየን፥ እንዲህ ያለ ነገርም በዚህ ጊዜ ባላሰማን ነበር” አለችው። 24 ሴቲቱም ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሶምሶን ብላ ጠራችው፤ እግዚአብሔርም ባረከው፤ ልጁም አደገ። 25 የእግዚአብሔርም መንፈስ በሶራሕና በእስታሔል መካከል ባለው በዳን ሰፈር ውስጥ ከእርሱ ጋር ይሄድ ጀመረ። |