ኢዮብ 42 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ኢዮብም መለሰ፥ እግዚአብሔርንም እንዲህ አለው፦ 2 “ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ የሚሳንህም እንደሌለ ዐወቅሁ። 3 ምክርን ከአንተ የሚሰውር፥ ቃሉንም ከአንተ የሚሸልግና የሚሸሽግ የሚመስለው ማን ነው? የማላስተውለውንና የማላውቀውንም ታላቅና ድንቅ ነገር የሚነግረኝ ማን ነው? 4 “ጌታ ሆይ፥ እባክህ፥ ስማኝ፥ እኔም ልናገር፤ እጠይቅህማለሁ፥ አንተም አስተምረኝ። 5 መስማትንስ ስለ አንተ ቀድሞ በጆሮዬ ሰምቼ ነበር፤ አሁን ግን ዐይኔ አየችህ፤ 6 ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ ሰውነቴም ቀለጠ። እኔ አፈርና አመድ እንደ ሆንሁ አውቃለሁ።” የኢዮብ ወዳጆች እንደ ተወቀሱ 7 እግዚአብሔርም ይህን ቃል ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ እግዚአብሔር ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፥ “እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ አንዲት ቅን ነገርን በፊቴ አልተናገራችሁምና አንተና ሁለቱ ባልንጀሮችህ በድላችኋል። 8 አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችንና ሰባት አውራ በጎችን ይዛችሁ ወደ ባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድ ሂዱ፥ እርሱም የሚቃጠልን መሥዋዕት ስለ ራሳችሁ ያሳርግላችሁ። ባሪያዬም ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልይ፥ እኔም ፊቱን እቀበላለሁ። ስለ እርሱ ባይሆን ባጠፋኋችሁ ነበር። በባሪያዬ በኢዮብ ላይ ቅን ነገርን በፊቴ አልተናገራችሁምና።” 9 ቴማናዊውም ኤልፋዝ፥ አውኬናዊው በልዳዶስና፥ አሜናዊው ሶፋር ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ፤ ስለ ኢዮብም ሲል ኀጢአታቸውን ይቅር አላቸው። የኢዮብ ጤናና ሀብት እንደ ተመለሰ 10 እግዚአብሔርም ኢዮብን አዳነው። ኢዮብም ስለ ወዳጆቹ ጸለየ፥ እግዚአብሔርም ኀጢአታቸውን ተወላቸው፤ እግዚአብሔርም ቀድሞ በነበረው ገንዘቡ ሁሉ ፋንታ ሁለት እጥፍ ከዚያም በላይ አድርጎ ለኢዮብ ሰጠው። 11 ወንድሞቹና እኅቶቹ ቀድሞም ያውቁት የነበሩት ሁሉ የሆነውን ሁሉ በሰሙ ጊዜ ወደ እርሱ መጡ፥ በቤቱም ከእርሱ ጋር እንጀራ በሉ፥ ጠጡም፤ አጽናኑትም፤ እግዚአብሔርም ባመጣበት ክፉ ነገር ሁሉ አደነቁ፤ እያንዳንዳቸውም ጥማድ በሬ፥ አራት ድራህማ የሚመዝን ወርቅና ብር ሰጡት። 12 እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን ለኢዮብ ባረከ፤ መንጋዎቹም ዐሥራ አራት ሺህ በጎች፥ ስድስት ሺህም ግመሎች፥ አንድ ሺህም ጥማድ በሬዎች፥ አንድ ሺህም እንስት አህዮች ነበሩ። 13 ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ተወለዱለት። 14 የመጀመሪያይቱን ስም ዕለት፥ የሁለተኛይቱንም ስም ቃስያ፥ የሦስተኛይቱንም ስም አማልትያስቂራስ ብሎ ሰየማቸው። 15 ከሰማይ በታች እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆች ያሉ የተዋቡ ሴቶች በሀገሩ ሁሉ አልተገኙም፤ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋር ርስት ሰጣቸው። 16 ኢዮብም ከደዌው ከዳነ በኋላ መቶ ሰባ ዓመት ኖረ፥ ኢዮብም የኖረበት ዘመን ሁሉ ሁለት መቶ አርባ ነው። ልጆቹንና የልጅ ልጆቹንም እስከ አራት ትውልድ ድረስ አየ። 17 ኢዮብም ሸምግሎ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ። 18 እግዚአብሔር ከሚያነሣቸው ሰዎች ጋር ዳግመኛ እንደሚነሣ የተጻፈ ነው። 19 ይህ ሰው በሶርያው መጽሐፍ እንደዚህ ተገልጦአል። የኖረበትም ሀገሩ በኤዶምያስና በዐረብ አውራጃ ያለ አውስጢድ ነው። 20 ስሙም ቀድሞ ኢዮባብ ነበረ፥ ዐረባዊት ሴትንም አገባ። ስሙ ሄኖን የሚባል ልጅንም ወለደችለት። እርሱም የኤሳው የልጅ ልጅ የዛራ ልጅ ነው። እናቱም ባሱራስ ትባል ነበር። 21 እርሱም ከአብርሃም አምስተኛ ነው። እርሱም በገዛት ሀገር በኤዶምያስ የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ነበሩ። 22 አስቀድሞ የነገሠ የቢዖር ልጅ ባላቅ ነው። የከተማዋም ስም ዲናባ ነበር። 23 ከባላቅም በኋላ ስሙ ኢዮብ ይባል የነበረው ኢዮባብ ነገሠ። ከእርሱም በኋላ በቴማን ሀገር የነገሠ አሶም ነበር። 24 ከእርሱም በኋላ በሞዓብ ምድረ በዳ የምድያምን ሰዎች የገደላቸው የበራድ ልጅ አዳድ ነበር፥ የከተማውም ስም ጌቴም ነበር። 25 ወደ እርሱ የመጡ ወዳጆቹም አንዱ ከዔሳው ልጆች የተወለደ በቴማኖን የነገሠው ኤልፋዝ፥ በአውኪኒዮን የተሾመው በልዳዶስና የአሜኔዎን ንጉሥ ሶፋር ነበሩ። |