ኢዮብ 38 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር ለኢዮብ እንደ መለሰለት 1 ኤልዩስ ንግግሩን ካቆመ በኋላ እግዚአብሔር በደመናና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ኢዮብን ጠየቀው፤ እንዲህም አለው፦ 2 “ከእኔ ምክርን የሚሸሽግ፥ በልቡም ነገርን የሚደብቅ ማን ነው? ከእኔ ይሰውረዋልን? 3 እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም መልስልኝ። 4 ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆነ ንገረኝ። 5 ብታውቅ መስፈሪያዋን የወሰነ፥ በላይዋስ የመለኪያ ገመድን የዘረጋ ማን ነው? 6 መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው? 7 ከዋክብት በተፈጠሩ ጊዜ መላእክቴ ሁሉ በታላቅ ድምፅ አመሰገኑኝ 8 ከእናቷ ማኅፀን በወጣች ጊዜ፥ ባሕርን በመዝጊያዎች ዘጋኋት፤ 9 ደመናውን ልብስ አደረግሁላት። በጭጋግም ጠቀለልኋት። 10 ድንበርም አደረግሁላት። መወርወሪያዎችንና መዝጊያዎችንም አኖርሁ። 11 እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ ከወሰንሽም አትለፊ፤ ነገር ግን ማዕበልሽ በመካከልሽ ይገደብ አልኋት። 12 “የንጋት ወገግታ በአንተ ተፈጥሮአልን? የአጥቢያ ኮከብስ ትእዛዙን በአንተ ዐውቋልን? 13 የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥ ከእርስዋም ኃጥኣንን ያናውጥ ዘንድ። 14 አንተ ጭቃውን ከመሬት ወስደህ ሕያው ፍጥረትን ፈጥረሃልን? በምድርስ ላይ እንዲናገር አድርገሃልን? 15 የኃጥኣንን ብርሃናቸውን ከልክለሃልን? የትዕቢተኞችንስ ክንድ ሰብረሃልን? 16 ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን? በጥልቁስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን 17 ከግርማህስ የተነሣ የሞት በሮች ተከፍተውልሃልን? የሲኦል በረኞችስ አንተን አይተው ይደነግጣሉን? 18 ከሰማይ በታች ያለ የምድርንስ ስፋት አስተውለሃልን? መጠኑም ምን ያህል እንደ ሆነ እስኪ ንገረኝ! 19 “የብርሃን ማደርያው ቦታ የት ነው? የጨለማስ ቦታው ወዴት አለ? 20 ትችል እንደ ሆነ፥ መንገዳቸውንም ታውቅ እንደሆነ፥ ወደ ዳርቻቸው እስኪ ውሰደኝ። 21 በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥ የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፥ በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም። 22 በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን? 23 ይህስ በጠላትህ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን ይጠበቅልሃልን? 24 አመዳይ ከየት ይወጣል? ከሰማይ በታች ያለ የአዜብ ነፋስስ እንዴት ይበተናል? 25 ለኀይለኛው ዝናብ መውረጃውን፥ ወይስ ለሚያንጐዳጕደው መብረቅ መንገድን ያዘጋጀ ማንነው? 26 ማንም በሌለበት ምድር ላይ፥ ሰውም በማይኖርበት ምድረ በዳ ይዘንም ዘንድ፥ 27 ባድማውንና ውድማውን ያጠግብ ዘንድ፥ ሣሩንም በምድረ በዳ ያበቅል ዘንድ፥ 28 የዝናብ አባቱ ማን ነው? ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው? 29 በረዶስ ከማን ማኅፀን ይወጣል? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው? 30 እርሱም እንደ ፈሳሽ ውኃ ይወርዳል። ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥ የኃጥኣንንስ ፊት ማን አዋረደ? 31 “በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን? 32 ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥ ወይስ የምሽቱን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን? 33 የሰማይን ሥርዐት፥ ከሰማይ በታችስ የሚሆነውን ታውቃለህን? 34 ደመናውን በቃልህ ትጠራዋለህን? ብዙ ውኃስ እየተንቀጠቀጠ ይመልስልሃልን? 35 መብረቁን ትልከዋለህን? እርሱስ ይሄዳልን? ደስታህስ ምንድን ነው ይልሃልን? 36 ለሴቶች የፈትልን ጥበብና የተለያዩ የጥልፍ ሥራዎችን ዕውቀት ማን ሰጠ? 37 የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ሰማይንም ወደ ምድር ያዘነበለ ማን ነው? 38 እንደ ትቢያ በምድር ተዘርግቷል፤ እንደ ዓለት ድንጋይም አጣበቅሁት። 39 “ለአንበሳዪቱ አደን ታድናለህን? የእባቦችንስ ነፍስ ታጠግባለህን? 40 በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው በጫካም ውስጥ አድብተው ይቀመጣሉና። 41 ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥ የሚበሉትም ፈልገው ሲቅበዘበዙ፥ ለቍራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው? |