ኢዮብ 37 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “ስለዚህም ልቤ ደነገጠችብኝ፥ ከስፍራዋም ተንቀሳቀሰች። 2 የእግዚአብሔርን የቍጣውን ድምፅ ስማ፥ ከአፉም የሚወጣውን ጕርምርምታ አድምጥ። 3 እርሱን ወደ ሰማያት ሁሉ ታች፥ ብርሃኑንም ወደ ምድር ዳርቻ ይሰድዳል። 4 በስተኋላው ድምፅ ይጮኻል፤ በግርማውም ድምፅ ያንጐደጕዳል፤ ድምፁም በተሰማ ጊዜ ሰዎች እንዲጠፉ አያደርግም። 5 ኀያሉ እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅ አድርጎ ያንጐደጕዳል፤ ለእንስሳት በየጊዜው ምግባቸውን ያዘጋጃል፥ የሚተኙበትንም ጊዜ ያውቃሉ፤ በዚህ ሁሉ ልብህ አይደንግጥብህ፤ ሥጋህም ልብህም ከግዘፉ አይለወጥብህ፤ እርሱም እኛ የማናውቀውን ታላቅ ነገር ያደርጋል። 6 በረዶውንና ውሽንፍሩን፥ ብርቱውንም ዝናብ በምድር ላይ እንዲወርድ ያዝዛል። 7 ሰው ሁሉ ደካማነቱን ያውቅ ዘንድ፥ የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል። 8 አውሬዎቹም ወደ ጫካው ይገባሉ፥ በዋሾቻቸውም ያርፋሉ። 9 ከተሰወረ ማደሪያውም ችግር፥ ከተራሮች ጫፍም ብርድ ይመጣል። 10 ከኀያሉ እግዚአብሔር እስትንፋስ ውርጭ ይመጣል። ውኃውንም እንደ ወደደ ይመራዋል። 11 የተመረጡትን በደመና ይሰውራል፤ ብርሃኑም ደመናውን ይበትናል፤ 12 እርሱም ሰው በሚኖርበት ዓለም ላይ፥ ያዘዘውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ፥ ፈቃዱ ወደ መራችው ይዞራል። 13 ይኸውም፥ ለተግሣጽ ወይም ለምድሩ ወይም በምሕረት ለሚያገኘው እንዲሆን ነው። 14 “ኢዮብ ሆይ፥ ይህን ስማ፤ ቁም፥ በእግዚአብሔርም ኀይል ተገሠጽ። 15 እግዚአብሔር ሥራውን እንዳከናወነ ከጨለማም ለይቶ ብርሃንን እንደ ፈጠረ እናውቃለን። 16 የደመናትን ክፍሎች፥ አስፈሪ የሆነውንም የኀጢአተኞችን አወዳደቅ ያውቃል። 17 የአዜብ ነፋስ በተኮሰ ጊዜ ያንተ ልብስህ የሞቀ ነው። እንግዲህ በምድር ላይ ፀጥ በል። 18 እንደ ቀለጠ መስተዋት ብርቱ የሆኑትን ሰማያት ከእርሱ ጋር ልትዘረጋ ትችላለህን? 19 ስለዚህ ንገረኝ! ምን እንለዋለን? እንግዲህ ዝም እንበል፥ ብዙም አንናገር፥ 20 “ሰው በእኔ ዘንድ ሲቆም ዝም እል ዘንድ፥ መጽሐፍ ወይም ጸሓፊ አለኝን? 21 “ብርሃን ለሁሉ የሚታይ አይደለም ብርሃን በእርሱ ዘንድ በደመና ውስጥ ሆኖ ከሩቅ በሰማያት ያበራል። 22 ከሰሜን እንደ ወርቅ የሚያበራ ደመና ይወጣል፤ በዚህም ሁሉን የሚችል የእግዚአብሔር ታላቅ ክብርና ምስጋና አለ። 23 በኀይል ከእርሱ ጋር እኩል የሚሆን፥ እውነትንም የሚፈርድ ሌላ አናገኝም። እርሱ እንደማይሰማ ታስባለህን? 24 ስለዚህ ሰዎች ይፈሩታል፤ በልባቸውም ጠቢባን የሆኑ ሁሉ ይፈሩታል።” |