ኢዮብ 36 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኤልዩስ መጨረሻ ንግግር 1 ኤልዩስም ደግሞ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “ገና የምናገረው ነገር አለኝና ጥቂት ታገሠኝ፥ እኔም አስተምርሃለሁ። 3 ዕውቀቴን ከሩቅ አመጣለሁ፥ ሥራዬንም እውነት ነው እላለሁ። 4 ቃሌ ሐሰት ያይደለ እውነት ነው። አንተም የዐመፅ ቃላትን አትሰማም። 5 “በጥበብ ብርቱና ኀያል የሆነ እግዚአብሔር፥ የዋሁን ሰው እንደማይጥለው ዕወቅ። 6 እርሱ የበደለኞችን ሕይወት አያድንም፤ ለችግረኞች ግን ፍርዱን ይሰጣል። 7 ዐይኑን ከጻድቃን ላይ አያርቅም፤ ለዘለዓለም ከነገሥታት ጋር በዙፋን ላይ ያስቀምጣቸዋል፥ በድል አድራጊነትም ያኖራቸዋል። እነርሱም ከፍ ከፍ ይላሉ። 8 በሰንሰለት እጃቸውን የታሠሩ በችግር ገመድ ይያዛሉ። 9 ሥራቸውንና መተላለፋቸውን ይነግራቸዋል፥ ብዙ ነውና። 10 ጻድቃንን ግን ይሰማቸዋል፥ ከኀጢአትም ይመለሱ ዘንድ ያዝዛቸዋል። 11 ቢሰሙና ቢያገለግሉትም፥ ዕድሜአቸውን በመልካም፥ ዘመናቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ። 12 ኃጥኣንን ግን አያድናቸውም እግዚአብሔርን ያዩ ዘንድ አይወዱምና፥ ሲገሥፃቸውም አይሰሙምና። 13 “ግብዞች ግን በልባቸው ቍጣን ያዘጋጃሉ፤ እርሱም ባሰራቸው ጊዜ አይጮኹም። 14 ስለዚህም በሕፃንነታቸው ሳሉ ሰውነታቸው ትጠፋለች፥ ሕይወታቸውንም መላእክት ያጠፉአታል። 15 የተቸገረውንና ረዳት የሌለውን አስጨንቀዋልና፥ የየዋሃንንም ፍርድ ለውጠዋልና። 16 አንተን ግን ከጠላትህ አፍ አድኖሃል፥ በበታችህም ጥልቅ ባሕር፥ ፈሳሽ ምንጭም አለ፥ ማዕድህም በስብ ተሞልታ ትወርዳለች። 17 ፍርድን ለጻድቃን አያዘገይምና። 18 ይበድሉ ዘንድ በተቀበሉት መማለጃ ኀጢአት ምክንያት ቍጣ በኃጥኣን ላይ ትመጣለች። 19 በጭንቀት ካሉ ከችግረኞች ልመና የተነሣ አእምሮህ በፈቃድ አያስትህ 20 በእነርሱ ፋንታ ወገኖች እንዲገቡ፥ ኀያላን ሰዎችን ሁሉ በሌሊት አታስወጣ። 21 መልካምን አድርግ እንጂ፥ ክፉን እንዳትሠራ ተጠንቀቅ። ስለዚህም ከችግር ትድናለህ። 22 “እነሆ፥ ኀያሉ እግዚአብሔር በኀይሉ ያጸናል። እንደ እርሱስ ያለ ኀያል ማን ነው? 23 ሥራውንስ የሚመረምር ማን ነው? ወይስ፦ ክፉ ሠርተሃል የሚለው ማን ነው? 24 ሰዎች ሊሠሩት ከሞከሩት በላይ፥ ሥራው ታላቅ እንደ ሆነ አስብ። 25 ሰው ሁሉ ራሱ፥ ኃጥኣን ሙታን እንደ ሆኑ ያስባል። 26 እነሆ፥ ኀያሉ እግዚአብሔር ታላቅ ነው፥ እኛም አናውቀውም፤ የዘመኑም ቍጥር አይመረመርም። 27 የዝናቡም ነጠብጣቦች በእርሱ ይቈጠራሉ። ዝናብም ከደመና ይንጠባጠባል፤ 28 የጥንቱ ይበቅላል። ደመናም በሟች ላይ ይጋርዳል፥ ስፍር ቍጥር የሌለው ዝናብ ይዘንባል፥ 29 አንድ ሰው የደመናውን መዘርጋት፥ ወይም የማደሪያውን ልክ ቢያውቅ፥ 30 እነሆ፥ በዙሪያው ብርሃኑን ይዘረጋል የባሕሩንም ጥልቀት ይከድነዋል። 31 በእነዚህ በአሕዛብ ላይ ይፈርዳል፤ ለኀይለኛውም ምግቡን ይሰጠዋል። 32 በእጁ ብርሃንን ይሰውራል፥ አደጋ የሚጥልባትንም አዘዘ። 33 ስለ እርሱም ወዳጁ፥ በዐመፃው ያገኘችውን ይናገራል። |