ኢዮብ 35 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኢዮብ ራሱን በማጽደቁ ኤልዩስ እንደ ተቃወመ 1 ኤልዩስም ደግሞ መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “አንተ ተዋቅሰህ ምን ትላለህ? ወይስ፦ በእግዚአብሔር ፊት እኔ ጻድቅ ነኝ የምትል አንተ ማን ነህ? 3 ኀጢአት ብሠራስ ምን አደርጋለሁ? ትላለህ። 4 እኔ ለአንተና ለሦስቱ ወዳጆችህ እመልሳለሁ። 5 ወደ ሰማይ ተመልከት፥ እይም፤ ደመናም ከአንተ በላይ ምን ያህል ከፍ እንዳለ ዕወቅ። 6 ኀጢአት ብትሠራ በእርሱ ላይ ምን ታደርጋለህ? ብዙም ብትበድል ምን ማድረግ ትችላለህ? 7 ጻድቅስ ብትሆን ምን ትሰጠዋለህ? ወይስ ከእጅህ ምንን ይቀበላል? 8 እንደ አንተ ያለውን ሰው ክፋትህ ይጎዳዋል፤ ለሰውም ልጅ ጽድቅህ ይጠቅመዋል። 9 ከግፈኞች ብዛት የተነሣ ሰዎች ይጮኻሉ፤ ከብዙዎች ክንድ የተነሣም ለርዳታ ይጠራሉ። 10 ነገር ግን በሌሊት ጥበቃን የሚያዝዝ ፈጣሪዬ እግዚአብሔር ወዴት ነው? የሚል የለም፤ 11 እርሱም ከምድር እንስሶች ይልቅ፥ ከሰማይም ወፎች ይልቅ የሚለየኝ ነው። 12 በዚያ ስለ ክፉ ሰዎች ስድብ ይጮኻሉ፥ እርሱ ግን አይሰማቸውም። 13 እግዚአብሔር በእውነት ክፉ ነገርን ሊያይ አይወድም። እርሱ ሁሉን የሚችል ዐዋቂ አምላክ ነውና። 14 ክፉ የሚሠሩትን አይሰማቸውም፥ እኔንም ያድነኛል፤ አንተ አሁን የሚቻል እንደ መሆኑ መጠን ልታመሰግነው ትችል እንደ ሆነ እስኪ በፊቱ ተዋቀስ። 15 አሁን ቍጣውን የሚያውቅ የለምና፥ ታላቅ ኀጢአቱንም የሚያስብ የለምና። 16 ኢዮብ ግን አፉን በከንቱ ይከፍታል፥ ያለ ዕውቀትም ቃሉን ያበዛል።” |