ኢዮብ 33 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ኤልዩስ ኢዮብን እንደ ገሠጸው 1 “ነገር ግን፥ ኢዮብ ሆይ፥ ቃሌን ስማ፥ ነገሬንም አድምጥ። 2 እነሆ፥ አፌን ከፍቻለሁ፥ አንደበቴም ይናገራል። 3 ልቤም ንጹሕ ነገርን ያስባል፥ የከንፈሮችም ማስተዋል ንጹሕ ነገርን ይመረምራል። 4 የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ያስተምረኛል። 5 በዚህ ነገር ልትመልስልኝ ትችል እንደ ሆነ ታገሠኝ፥ እኔም እነግርሃለሁ፤ አንተም መልስልኝ። 6 አንተ እንደ እኔ ከጭቃ የተፈጠርህ ነህ፥ የሁላችንም ተፈጥሮ ከዚያው ነው። 7 እነሆ፥ ግርማዬ አታስፈራህም፥ እጄም አትከብድብህም። 8 ግፍህን ተናግረሃል፥ የቃልህንም ድምፅ ሰምቻለሁ፥ እንዲህም ብለሃል፦ 9 እኔ ንጹሕ ነኝ፥ አልበደልሁምና፤ እኔ ጻድቅ ነኝ፥ ኀጢአትንም አልሠራሁም። 10 እነሆ፥ ምክንያት አግኝቶብኛል፥ እንደ ጠላትም ቈጥሮኛል፤ 11 እግሬን በግንድ አጣበቀ፥ መንገዴንም ሁሉ ጠበቀ። 12 እነሆ፥ እኔ ጻድቅ ነኝ፥ ቃሌንም አይሰማኝም እንዴት ትላለህ? ከሟች ሰው በላይ ያለ እርሱ ዘለዓለማዊ ነውና። 13 አንተ፦ ‘ቃሌን ሁሉ ለምን አይሰማኝም?’ ትላለህ። 14 እግዚአብሔር በሕልም ወይም በሌሊት ራእይ፥ አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ የተናገረ እንደሆነ፥ 15 በአልጋ ላይ ተኝተው ሳሉ፥ በሰዎች ላይ ታላቅ ድንጋጤን ያመጣል። 16 በዚያን ጊዜ የሰዎችን ማስተዋል ይከፍታል፥ ግርማ ባለው ራእይም ያስደነግጣቸዋል፤ 17 ሰውን ከኀጢአቱ ይመልሰው ዘንድ፥ ሥጋውንም ከውድቀት ያድነው ዘንድ፥ 18 ነፍሱን ከሞት ያድናታል፤ በሰይፍም እንዳይጠፋ ይጠብቀዋል። 19 “ደግሞ በአልጋ ላይ በደዌ ይገሥጸዋል፥ አጥንቱም ሁሉ ይንቋቋል። 20 ማንኛውንም መብል መቅመስ አይችልም። ሰውነቱ ግን መብልን ትበላ ዘንድ ትመኛለች። 21 ሥጋው እስከሚያልቅ ድረስ፥ አጥንቱም ባዶውን እስከሚታይ ድረስ፥ 22 ሰውነቱ ለሞት፥ ሕይወቱም ወደ ሲኦል ቀርባለች። 23 የሞት መላእክት ምንም ሺህ ቢሆኑ፥ በልቡ ወደ እግዚአብሔር ሊመለስ ቢያስብ፥ ኀጢአቱን ለሰው ቢናገር፥ በደሉንም ቢገልጥ፥ ከእነርሱ አንዱ እንኳ አይገድለውም፤ 24 በሞት እንዳይጠፋ ይጠብቀዋል፥ ሰውነቱንም እንደ ግድግዳ ምርግ ያድሳታል። አጥንቶቹንም በመቅን ይሞላል። 25 ሥጋውን እንደ ሕፃን ሥጋ ያለመልማል፤ ከሰዎችም ይልቅ ወደ ጕብዝናው ዘመን ይመልሰዋል። 26 ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፥ ጸሎቱም ተቀባይነትን ያገኛል። በደስተኛም ፊት እያመሰገነ ይገባል፥ ለሰውም ጽድቁን ይመልስለታል። 27 ያንጊዜም ሰው ራሱን ይነቅፋል፤ እንዲህም ይላል፦ ‘እኔ ምን አድርጌአለሁ? እንደ ኀጢአቶችም መጠን አልቀጣኝም፤ 28 ነፍሴ ወደ ጥፋት እንዳትወርድ አድኖአታል፥ ሕይወቴም ብርሃንን ታያለች።’ 29 “እነሆ፦ ሁሉን የሚችል እርሱ፥ ይህን ሁሉ ሦስት ጊዜ ከሰው ጋር ያደርጋል፤ 30 ሕይወቴም በብርሃን ውስጥ ታመሰግን ዘንድ፥ እርሱ ነፍሴን ከሞት አድኖአታል። 31 ኢዮብ ሆይ፥ አድምጥ፥ እኔንም ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም እናገራለሁ። 32 ነገር ቢኖርህ ተናገር፤ ትጸድቅ ዘንድ እወድዳለሁና ተናገር። 33 ያለዚያም እኔን ስማ፤ ዝም በል፥ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።” |