ኢዮብ 31 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ፥ ድንግሊቱንም አልተመለከትሁም፤ 2 የእግዚአብሔር እድል ፋንታ ከላይ፥ ሁሉንም የሚችል የአምላክ ርስት ከአርያም ምንድን ነው? 3 ሞት ለዐመፀኛ፥ መለየትም ኀጢአትን ለሚሠሩ ነው። 4 እርሱ መንገዴን የሚያይ አይደለምን? እርምጃዬንስ ሁሉ የሚቈጥር አይደለምን? 5 ከፌዘኞች ጋር ሄጄ እንደ ሆነ፥ እግሬም ከመንገዱ ገለል ብላ እንደ ሆነ፥ 6 በእውነተኛ ሚዛን ልመዘን፥ እግዚአብሔርም ቅንነቴን ያውቃል። 7 እርምጃዬ ከመንገዱ ፈቀቅ ብሎ እንደ ሆነ፥ ልቤም ዐይኔን ተከትሎ እንደ ሆነ፥ ጉቦም በእጄ ተጣብቆ እንደ ሆነ፥ 8 እኔ ልዝራ፥ ሌላ ሰውም ይብላው፤ በምድር ላይ ሥሬ ይነቀል። 9 ልቤ ወደ ሌላ ወንድ ሚስት ተከትሎ እንደ ሆነ፥ በደጅዋም አድብቼ እንደ ሆነ፥ 10 ሚስቴ ሌላውን ሰው ደስ ታሰኝ። ልጆቼም ይዋረዱ። 11 የሌላውን ወንድ ሚስት ማርከስ፥ የማይቈጣጠሩት የቍጣ መቅሠፍት ነው። 12 ይህ በሕዋሳት ሁሉ የሚነድድ እሳት፥ የገባበትንም ሁሉ ከሥር የሚነቅል ነውና። 13 “ወንድ ባሪያዬ ወይም ሴት ባሪያዬ በእኔ ዘንድ በተምዋገቱ ጊዜ፥ ፍርዳቸውን አዳልቼ እንደ ሆነ፥ 14 እግዚአብሔር በመረመረኝ ጊዜ ምን አደርጋለሁ? በጐበኘኝ ጊዜስ በፊቱ ምን እመልስለታለሁ? 15 እኔን በማኅፀን የፈጠረ እነርሱንስ የፈጠረ አይደለምን? በማኅፀንስ ውስጥ የሠራን አንድ አይደለምን? 16 “ድሆች የሚሹትን እንዳያገኙ አድርጌ እንደ ሆነ፥ የመበለቲቱንም ዐይን አጨልሜ እንደ ሆነ፥ 17 እንጀራዬን ለብቻዬ በልቼ እንደ ሆነ፥ ለድሃአደጉም ደግሞ ከእርሱ አላካፈልሁ እንደ ሆነ፥ 18 እርሱን ከታናሽነቱ ጀምሮ እንደ አባቱ ከእኔው ጋር አሳድጌው ነበር፤ ከእናቱም ማኅፀን ከተወለደ ጀምሮ አሳደግሁት። 19 ራቁቱን የሆነው ሰው በብርድ ሲሞት አይቼ፥ አላለበስሁት እንደ ሆነ፥ 20 ድሆች አልመረቁኝ እንደ ሆነ፥ በበጎቼም ጠጕር ትከሻቸው አልሞቀ እንደ ሆነ፥ 21 ብዙ ረዳት እንዳለኝ ተማምኜ በድሃአደጉ ላይ እጄን አንሥቼ እንደ ሆነ፥ 22 ትከሻዬ ከመሠረቷ ትውደቅ፥ ክንዴም ከመገናኛዋ ትሰበር። 23 የእግዚአብሔር ግርማ አስደንግጦኛልና፤ በእርሱም ከመያዝ በምክንያት ማምለጥ አልቻልሁም። 24 “ወርቄን በመሬት ውስጥ ቀብሬ እንደ ሆነ፥ ዋጋው ብዙ በሆነ ዕንቍ ታምኜም እንደ ሆነ፥ 25 ሀብቴ በበዛ ጊዜ፥ ደስ ብሎኝ እንደ ሆነ፥ ስፍር ቍጥር በሌለውም መዝገብ ላይ እጄን ጨምሬ እንደ ሆነ፥ 26 የሚያበራ ፀሐይ እንደሚጠፋ ጨረቃም እንደምትጨልም አላይምን? በራሳቸው ለመኖር ኀይል የላቸውምና፥ 27 ልቤ በስውር ተታልሎ እንደ ሆነ፥ በአፌም ላይ እጄን አኑሬ ስሜ እንደ ሆነ፥ 28 በልዑል እግዚአብሔር ፊት በዋሸሁ ነበርና ይህ ደግሞ ትልቅ በደል ይሁንብኝ። 29 በጠላቴ ውድቀት ደስ ብሎኝ እንደ ሆነ፥ በልቤም እሰይ ብዬ እንደ ሆነ፥ 30 ጆሮዬ መርገሜን ትስማ፤ በወገኔም መካከል ክፉ ስም ይውጣልኝ። 31 “ቤተ ሰቦቼ እኔ ስራራላቸው፥ ሥጋውን እንበላ ዘንድ ማን በሰጠን ብለው እንደ ሆነ፥ 32 መጻተኛው ግን በሜዳ አያድርም ነበር፥ ደጄንም ለመጣው ሁሉ እከፍት ነበር፤ 33 ታላቅ በደልም በድዬ እንደ ሆነ፥ ኀጢአቴንም ሰውሬ እንደ ሆነ፥ 34 ከብዙ ሕዝብ የተነሣ በፊታቸው ለመናገር አፍሬ እንደ ሆነ፥ ድሃውም ከደጄ ባዶውን ወጥቶ እንደ ሆነ፥ 35 የሚያደምጠኝን ማን በሰጠኝ! የእግዚአብሔርንም እጅ አልፈራሁ እንደ ሆነ፥ የሚያስፈርድብኝ የክስ ጽሑፍ ምነው በኖረኝ! 36 በትከሻዬ ላይ እሸከመው ነበር፥ አክሊልም አድርጌ በራሴ አስረው ነበር፥ በብዙዎችም መካከል አነብበው ነበር፤ 37 ከባለ ዕዳዬ የምቀበለው ሳይኖር ቀድጀው እመለሳለሁ። 38 “እርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ እንደ ሆነ፥ ትልሞችዋም በአንድ ላይ አልቅሰው እንደ ሆነ፥ 39 ፍሬዋን ለብቻዬ ያለ ዋጋ በልቼ እንደ ሆነ፥ ባለ መሬቱንም አባርሬ ነፍሱን አሳዝኜ እንደ ሆነ፥ 40 በስንዴ ፋንታ እንክርዳድ፥ በገብስም ፋንታ ኵርንችት ይብቀልብኝ።” ኢዮብም ነገሩን ፈጸመ። |