ኢዮብ 29 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢዮብ መጨረሻ ንግግር 1 ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “እግዚአብሔር ይጠብቀኝ እንደ ነበረው ጊዜ፥ ወደ ፊተኛው ወራት ማን በመለሰኝ? 3 በራስጌዬ ላይ መብራቴ በበራ ጊዜ፥ እኔም ጨለማውን ዐልፌ በብርሃኑ በሄድሁ ጊዜ፥ 4 በበረከት ሁሉ በነበርሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔርም ቤቴን በጐበኘ ጊዜ፥ 5 ባለ ሀብት በነበርሁ ጊዜ፥ ልጆችም በዙሪያዬ በነበሩ ጊዜ፥ 6 ቅቤ በመንገዴ ይፈስስ በነበረ ጊዜ፥ ወተት በተራራዬ ይፈስስልኝ በነበረ ጊዜ። 7 ወደ ከተማዪቱ ገሥግሼ በወጣሁ ጊዜ፥ በአደባባዩም ወንበሬን ባኖሩልኝ ጊዜ፥ 8 ጐበዛዝት እኔን አይተው ተሸሸጉ፥ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ቆሙ። 9 ኀያላኑም ከመናገር ዝም አሉ፥ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ጫኑ። 10 የሰሙኝም ብፁዕ ይሉኛል። ምላሳቸውም በትናጋቸው ተጠጋ። 11 የሰማችኝም ጆሮ ብፁዕ አለችኝ፥ ያየችኝም ዐይን ገለል አለች፤ 12 ድሃውን ከሚጨቁነው እጅ አድኛለሁና። ረዳት የሌለውን ደሃአደጉንም ረድቸዋለሁና። 13 ለሞት የቀረበው መረቀኝ፤ የባልቴቲቱም አፍ ባረከኝ፤ 14 ጽድቅን ለበስሁ፥ ቅንነትንም እንደ መጎናጸፊያ ተሸለምሁ፤ ፍርድንም እንደ ኩፋር ተቀዳጀኋት 15 ለዕውራን ዐይን፥ ለአንካሳዎችም እግር ነበርሁ። 16 ለድሃዎች አባት ነበርሁ፥ የማላውቀውንም ሰው ክርክር መረመርሁ። 17 የኀጢአተኞችን መንጋጋ ሰበርሁ፥ የነጠቁትንም ከጥርሳቸው ውስጥ አስጣልሁ። 18 እኔም እንደምሸመግልና እንደማረጅ፥ እንደ ረዥም ዘንባባም ረዥም ዘመን እንደምኖር፥ እንደ አሸዋም ዘመኔን እንደማበዛ ዐሰብሁ። 19 ውኃ በሥሬ ላይ ይፈስሳል፥ ጠልም በአዝመራዬ ላይ ይወርዳል፤ 20 ክብሬ በእኔ ዘንድ ታድሶአል፥ ቀስቴም በእጄ ውስጥ ሳለ እሄዳለሁ። 21 “ሰዎች እኔን ይሰሙኛል፥ ያዳምጡኝማል፥ በምክሬም ዝም ይላሉ። 22 በነገሬ ላይ ደግመው አይናገሩም፤ ባነጋገርኋቸውም ጊዜ ደስ ይላቸዋል። 23 የተጠማች ምድር ዝናምን ተስፋ እንደምታደርግ፥ እንደዚሁም እነርሱ ንግግሬን ይጠባበቃሉ። 24 በእነርሱ ብስቅ አያምኑም፤ የፊቴም ብርሃን አልወደቀም። 25 መንገዳቸውን መረመርሁ፤ እንደ አለቃም ሆኜ ተቀመጥሁ፤ ንጉሥ በሠራዊቱ መካከል እንደሚኖር ኖርሁ፤ በሚያዝኑም ጊዜ በእኔ ይጽናኑ ነበር። |