ኢዮብ 28 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “በእውነቱ ብር የሚወጣበት ቦታ አለ፥ ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ። 2 ብረትም ከመሬት ውስጥ ይወጣል፤ መዳብም እንደ ድንጋይ ይፈለጣል። 3 ለጨለማ ወሰንን ያደርጋል፤ እርሱ ሁሉን ይመረምራል፥ የጨለማንና የሞት ጥላ ድንጋይንም ይመረምራል። 4 በአፈር ምክንያት እንደሚከፈል ወንዝ የጽድቅን መንገድ የረሱ በኀጢአታቸው ይደክማሉ። ከሰዎችም መካከል ይለያሉ። 5 እንጀራ ከምድር ውስጥ ይወጣል፤ በእሳትም እንደሚሆን ታችኛው ይገለበጣል። 6 ድንጋይዋ እንደ ሰንፔር፥ ወርቅዋም እንደ አፈር የሆነ መሬት አለች። 7 መንገድዋን ዎፍ አያውቀውም፥ የንስርም ዐይን አላየውም። 8 የትዕቢተኞች ልጆች አልረገጡአትም፥ ደቦል አንበሳም በውስጥዋ አላለፈባትም። 9 ሰው ወደ ቡላድ ድንጋይ እጁን ይዘረጋል፥ ተራራዎችንም ከመሠረታቸው ይገለብጣቸዋል። 10 ከድንጋይ ውስጥ መንዶልዶያ ይወቅራል፤ ዐይኔም የከበረውን ነገር ሁሉ ታያለች። 11 የፈሳሹንም ጥልቀት ይገልጣል። ኀይሉንም በብርሃን ይገልጣል። 12 “ነገር ግን ጥበብ ወዴት ትገኛለች? የጥበብስ ሀገርዋ ወዴት ነው? 13 ሟች ሰው መንገድዋን አያውቅም፤ በሰዎችም ዘንድ አትገኝም። 14 ቀላይ፦ በእኔ ውስጥ የለችም ትላለች። ባሕርም፦ በእኔ ዘንድ የለችም ይላል። 15 ስለ እርስዋም ማንም ምዝምዝ ወርቅ አይሰጥም ብርም በእርስዋ ለውጥ አይመዘንም። 16 ከአፌር ወርቅም ጋር አትወዳደርም። በከበረ መረግድና በሰንፔር አትገመትም። 17 ወርቅና ብርጭቆ አይወዳደሩአትም፥ የወርቅም ጥሬ ዕቃ የእርስዋ ለውጥ አይሆንም። 18 ዛጎልና አልማዝ አይታሰቡም። አንተ ግን እጅግ ከከበሩ ነገሮች ሁሉ ይልቅ ጥበብን አቅርባት። 19 የኢትዮጵያ ሉል አይተካከላትም፥ በጥሩም ወርቅ አትገመትም። 20 “እንግዲያ ጥበብ ከወዴት ትገኛለች? የማስተዋልስ ሀገሯ ወዴት ነው? 21 በሰው ሁሉ ዘንድ ተረስታለች፥ ከሰማይ ወፎችም ተሰውራለች። 22 ሞትና ሲኦል ወሬዋን በጆሮቻችን ሰማን ብለዋል። 23 “እግዚአብሔር መንገድዋን አሳመረ፥ እርሱም ስፍራዋን ያውቃል። 24 እርሱም በሰማይ ያለውን ይመለከታል፥ በምድርም ያለውን ሁሉ ያውቃል። 25 ለነፋስ ሚዛንን ለውሆችም መስፈሪያን አደረገ። 26 እነዚህን በፈጠረ ጊዜ እንዲሁ ዐውቆ ቈጠራቸው። ለዝናም ሥርዐትን ለነጐድጓድ መብረቅም መንገድን አደረገ። 27 በዚያን ጊዜ አያት፥ ገለጣትም፤ አዘጋጃትም፥ አከበራት፥ ደግሞም መረመራት። 28 ሰውንም፦ ‘እነሆ፥ እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤ ከክፉ መራቅም ማስተዋል ነው’ ” አለው። |