ኢዮብ 27 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ኢዮብም ምሳሌውን ይመስል ዘንድ ደገመ እንዲህም አለ፦ 2 “እንደዚህ የፈረደብኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ነፍሴንም መራራ ያደረገ ሁሉን የሚችል ሕያው አምላክን! 3 እስትንፋሴ በእኔ ውስጥ ገና ሳለች፥ የሚያናግረኝም የእግዚአብሔር መንፈስ በአፍንጫዬ ውስጥ ገና ሳለ፥ 4 አንደበቴ ዐመፅን አይናገርም፤ ነፍሴም የዐመፅ አሳብን አትማርም፤ 5 እናንተን ማጽደቅ ከእኔ ዘንድ ይራቅ፤ እስክሞትም ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅምና። 6 ጽድቅን እየሠራሁ አልጠፋም፤ ያደረግሁት ክፉ ነገር አይታወቀኝምና። 7 ጠላቶች እንደ ኀጢአተኞች ውድቀት፥ በእኔ ላይም የሚነሡ እንደ በደለኞች ጥፋት ይሁኑ። 8 “ኀጢአተኛ ድኅነትን ተስፋ ያደርግ ዘንድ ለምን ደጅ ይጠናል? በእግዚአብሔርስ የማያምን ይድናልን? እንጃ! 9 በውኑ መከራ በመጣበትስ ጊዜ፥ ጸሎቱን ይሰማዋልን? 10 በእርሱ ዘንድስ ባለሟልነትን ያገኛልን? እግዚአብሔርንስ በጠራ ጊዜ ይመልስለታልን? 11 እኔ ግን በእግዚአብሔር እጅ ምን እንዳለ አስተምራችኋለሁ፤ ሁሉን በሚችል አምላክ ዘንድ ያለውንም አልዋሽም። 12 እነሆ፥ ሁላችሁም፥ በክፉዎች ላይ ክፋት እንደምትመጣባቸው ታውቃላችሁ። 13 ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ የኀጢአተኛ እድል ፋንታ ናት፥ ግፈኞችም ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ የሚቀበሏት ሀብት ናት። 14 ልጆቹ ቢበዙ ለጥፋት ይሆናሉ፤ ቢያድጉም ለማኞች ይሆናሉ። 15 ለእርሱም የቀሩት ፈጽመው ይሞታሉ። ለመበለቶቻቸውም የሚያዝንላቸው የለም። 16 እርሱ ብርን እንደ አፈር ቢሰበስብ፥ ወርቅንም እንደ ጭቃ ቢያዘጋጅ፥ 17 ይህን ሁሉ ጻድቃን ይወስዱታል። ሀብቱንም ቅኖች ይከፋፈሉታል። 18 ቤቱ እንደ ሸረሪት ድር፥ ቅንቅንም እንደሚበላው ይሆናል። 19 ባለጠጋ ይተኛል፥ የሚያነቃውም የለም፤ ዐይኖቹን ይከፍታል፥ ይደነቃልም። 20 ሥቃይ እንደ ጎርፍ ታገኘዋለች፤ በሌሊትም ዐውሎ ነፋስ ትነጥቀዋለች። 21 የሚያቃጥል ነፋስ ያነሣዋል፥ እርሱም ያልፋል፤ ከቦታውም ይጠርገዋል። 22 በእርሱም ላይ የማያውቀው ይመጣበታል፤ አይራራለትም፥ ከእጁም ፈጥኖ መሸሽ ይወድዳል። 23 በእርሱም እጁን ያጨበጭብበታል፤ ከስፍራውም በፉጨት ጎትቶ ያወጣዋል። |