ኢዮብ 24 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “እግዚአብሔር ዘመኖችን ለምን ረሳቸው? 2 ኃጥኣን የድንበሩን ምልክት አለፉ፤ እረኛውንም ከመንጋዎቹ ጋር ይነጥቃሉ። 3 የድሃአደጎቹን አህያ ይነዳሉ የመበለቲቱንም በሬ ስለ መያዣ ይወስዳሉ። 4 ደካሞችን ከእውነት መንገድ ያወጣሉ፤ የምድርም የዋሃን ሁሉ በአንድነት ይሸሸጋሉ። 5 እነሆ፥ በምድረ በዳ እንዳሉ እንደ ሜዳ አህዮች ሆኑ። ስለ እኔም ሥራቸውን ትተው ይወጣሉ፤ መብል፦ ከልጅነታቸው ጀምሮ ይጥማቸዋል። 6 “የራሳቸው ያልሆነውን እርሻ ያለ ሰዓቱ ያጭዳሉ። ኃጥኣን ድሆችን በወይናቸው ቦታ ያለ ዋጋና ያለ ቀለብ ያሠሩአቸዋል። 7 ብዙዎችን የተራቈቱትንም ያለ ልብስ ያሳድሩአቸዋል። መጐናጸፊያቸውንም ይገፍፏቸዋል። 8 በካፊያና ከተራሮች በሚወርድ ጠል ይረጥባሉ፤ መጠጊያም የላቸውምና ቋጥኙን ተተገኑ። 9 ድሃአደጉን ልጅ ከጡቱ ይነጥላሉ፤ ችግረኛውንም ያሠቃያሉ። 10 ችግረኞችን በደሉአቸው፥ ጣሉአቸውም፤ ከተራቡትም የሚጐርሱትን ነጠቋቸው። 11 በጠባብ ቦታ በዐመፅ ይሸምቃሉ፥ የጽድቅንም መንገድ አያውቁም። 12 ድሆችን ከከተማውና ከገዛ ቤቶቻቸው አባረሩአቸው የሕፃናትንም ነፍስ እጅግ አስጮሁ፤ 13 “እግዚአብሔር ግን እነዚህን ለምን አልገሠጻቸውም? በምድር ላይ ሳሉ አላስተዋሉም፥ የቅንነት መንገድንም አላዩም። በአደባባይዋም አልሄዱም። 14 ሥራቸውንም ዐውቆ ለጨለማ ዳረጋቸው። በሌሊትም እንደ ሌባ ናቸው። 15 የአመንዝራም ዐይን ድግዝግዝታን ይጠብቃል፦ የማንም ዐይን አያየኝም ይላል፥ ፊቱንም ይሸፍናል። 16 በጨለማ ቤቶችን ይነድላል፤ በቀን ይሸሸጋሉ፤ ብርሃንንም አያዩም። 17 የጥዋት ብርሃን ለእነርሱ ሁሉ እንደ ሞት ጥላ ነው፤ የሚሆነውን ድንጋጤ ያውቃሉና። ሞትንም ይጠራጠራሉና። 18 እርሱ በውኃ ፊት ላይ በርሮ ያልፋል፤ እድል ፋንታውም በምድር ላይ የተረገመች ናት፤ 19 ተክላቸው በምድር ላይ ሲደርቅ ያያሉ። ያላቸውም ድሀኣደጉን በዘበዙት። 20 ከዚህም በኋላ ኀጢአቱን ያስባል። እንደ ጤዛ ትነት ይጠፋል። እንደ ሥራውም ይከፈለዋል። ዐመፀኛም ሁሉ እንደ በሰበሰ ዛፍ ይሰበራል። 21 ለማትወልደው ለመካኒቱ በጎነትን አላደረገላትም፤ ለምትወልደውም አልራራም። 22 ነገር ግን ረዳት የሌላቸውን በቍጣው አጠፋቸው። እርሱም በተነሣ ጊዜ ሰው በሕይወቱ አይታመንም። 23 በታመመም ጊዜ መዳንን ተስፋ አያደርግም። ነገር ግን እርሱ በሕማሙ ይሞታል። 24 ከፍ ከፍ ባለ ጊዜም ብዙዎችን አስጨነቃቸው። እንደ አመድማዶ በሙቀት ይጠወልጋል። ከቃርሚያው እንደሚወድቅ እሸትም ይቈረጣል። 25 እንዲህስ ባይሆን ሐሰተኛ ነህ የሚለኝ፥ ነገሬንስ እንደ ኢምንት የሚያደርገው ማን ነው?” |