ኢዮብ 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢዮብ መልስ 1 ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦ 2 “ነፍሴን የምትነዘንዙአት፥ በቃላችሁስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው? ነገር ግን እግዚአብሔር ይህን እንዳደረገብኝ ዕወቁ፤ 3 ዐሥር ጊዜ ትናገሩኛላችሁ፥ ትሰድቡኛላችሁም፤ በሰውነቴ ላይ በጠላትነት ስትነሡብኝ አታፍሩም። 4 በእውነት እኔ ከበደልሁ፤ ስሕተቴ ከእኔ ጋር ትኖራለች። የማላውቀውንም ነገር ተናገርሁ፤ ነገሬም ስንፍና ነው እንጂ በየጊዜው አይደለም። 5 ወዮልኝ! አፋችሁን በእኔ ላይ ከፍ ከፍ ታደርጋላችሁና፤ ትጓደዱብኛላችሁ፤ ትዘልፉኛላችሁም። 6 እንግዲህ እግዚአብሔር እንደ አወከኝ፥ መዓቱንም በእኔ ላይ እንደ አበዛ ዕወቁ። 7 እነሆ፥ በዘለፋ እደክማለሁ፤ አልናገርምም፤ አሰምቼም እጮኻለሁ፤ ነገር ግን ፍርድ የለኝም። 8 ዙሪያዬ ታጥሯል፤ መተላለፊያም የለኝም፤ በፊቴም ጨለማን ጋርዶበታል። 9 ክብሬን ገፈፈኝ፤ ዘውዴንም ከራሴ ላይ ወሰደ። 10 በዚህና በዚያ አፈረሰኝ፤ እኔም ሄድሁ፤ ተስፋዬንም እንደ ዛፍ ቈረጠው። 11 በታላቅ ቍጣም ያዘኝ እንደ ጠላትም ቈጠረኝ። 12 ሠራዊቱ አብረው በእኔ ላይ መጡ፥ የሚሸምቁብኝም መንገዴን ከበቡ፥ 13 “ወንድሞች ተለዩኝ፥ ከእኔ ይልቅ ባዕዳንን ወደዱ። ጓደኞችም አላዘኑልኝም። 14 ዘመዶች አልተረዱኝም፥ ስሜንም የሚያውቁ ረሱኝ። 15 ቤተሰቦችና ሴቶች አገልጋዮች ሊያዩኝ አልፈቀዱም፤ እንደ መጻተኛም አስመሰሉኝ። 16 አገልጋዮችን እጠራቸዋለሁ፤ እነርሱ ግን ቸል ይሉኛል፤ በአፌም እለማመጣቸዋለሁ። 17 ሚስቴን እለማመጣታለሁ፤ እርስዋ ግን ትጠቃቀስብኛለች፤ የቤተሰቤንም ልጆች ፈጽሜ አቈላምጣቸዋለሁ። 18 ለዘለዓለም ተስፋ ቈረጡብኝ። ብነሣም በእኔ ላይ ሐሜት ይናገራሉ። 19 ያዩኝ ሁሉ ተጸየፉኝ፤ እኔ የምወድዳቸውም በላዬ ተነሡ። 20 ቍርበቴ ከሥጋዬ ጋር ይበጣጠሳል። አጥንቶቼም ይፋጩብኛል። 21 እናንተ ወዳጆቼ ሆይ፤ ማሩኝ፤ ማሩኝ፤ የእግዚአብሔር እጅ ዳስሳኛለችና። 22 ስለ ምን እናንተ እንደ እግዚአብሔር ታሳድዱኛላችሁ? ከሥጋዬስ ስለምን አትጠግቡም? 23 ቃሌን ማን በጻፈው! ማንስ በመጽሐፍ ውስጥ ለዘለዓለም ባተመው! 24 ማን በብረት ብርዕና በእርሳስ፥ በዓለት ላይ በቀረፀው! 25 እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደ ሆነ፥ በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፥ 26 ይህ ቍርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያ ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። 27 እኔ ራሴ አየዋለሁ፤ ዐይኖቼም ይመለከቱታል፤ ከእኔም ሌላ አይደለም። ሁሉም በብብቴ ተፈጸመ። 28 “በፊቱ ምን እንናገራለን? የነገሩ ሥርም በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥ 29 እናንተ ሐሣርን ፍሩአት፥ ቍጣ በኃጥኣን ላይ ይመጣልና፤ ያንጊዜም ክፋታቸው ከየት እንደ ሆነ ያውቃሉ።” |