ኢዮብ 17 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 ነፍሴን የሚያወጣት ያስጨንቀኛል መቃብርንም እመኘዋለሁ፤ ግን አላገኘውም፤ 2 እየለመንሁ ደከምሁ፤ ምንስ አደርጋለሁ? ባዕዳንም ገንዘቤን ሰረቁኝ። 3 ከእኔ ጋር አጋና የሚማታ ማን ነው? 4 ልባቸውንም ከጥበብ ሰውረኸዋል፤ ስለዚህ ከፍ ከፍ አታደርጋቸውም። 5 ለብዝበዛ ባልንጀሮቹን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው፥ የልጆቹ ዐይኖች ይጨልማሉ። 6 ለአሕዛብም ምሳሌ አደረግኸኝ፤ መሳቂያና መዘባበቻም ሆንኋቸው። 7 ዐይኖች ከእንባ የተነሣ ፈዘዙ፥ ሁሉም እጅግ ተጸየፉኝ። 8 ደስታዬን ተማምኛት ነበር፤ ነገር ግን ጠፋችብኝ፤ አግባብስ ወደ ኃጥኣን ትመለስ ዘንድ ነው። 9 ነገር ግን ወደ መንገዴ እንደ ምመለስ እተማመናለሁ፤ እጆችም የነጹ ናቸውና፤ ደስታዬን አገኛታለሁ። 10 ነገር ግን እናንተ ሁሉ ወደዚህ መጥታችሁ ታዩኛላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ እውነትን አላገኘሁምና። 11 “ዘመኖች በጩኸት አለቁ፤ የልቤ ሥርም ተቈረጠ። 12 ቀኑ ሌሊት ሆነብኝ። ከጨለማውም የተነሣ ብርሃኑ አጭር ነው። 13 ብዘገይም ሲኦል ቤቴ ናት፤ ምንጣፌም በጨለማ ተነጥፎአል። 14 ሞትን፦ አንተ አባቴ ነህ አልሁት፤ ትሎችንም እናንተ እናቴም ወንድሞቼም ናችሁ አልኋቸው። 15 እንግዲህ ተስፋዬ ወዴት ናት? ዳግመኛስ መልካም ነገርን አያታለሁን? 16 ከእኔስ ጋር ወደ መቃብር ትወርዳለችን? አብረንስ በመሬት ውስጥ እንቀበራለንን?” |