ኢዮብ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሶፋር ንግግር 1 አሜናዊው ሶፋር መለሰ፥ እንዲህም አለ፦ 2 “ብዙ እንደምትናገር እንዲሁ መስማት አለብህ። ወይስ በንግግርህ ብዛት ጻድቅ የምትሆን ይመስልሃልን? ከሴቶች የሚወለድ ዘመኑ ጥቂት የሆነ ቡሩክ ነው። 3 ንግግር አታብዛ፤ የሚከራከርህ የለምና። 4 አንተ፦ በሥራዬ ንጹሕ ነኝ በፊቱም ጻድቅ ነኝ አትበል። 5 ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ! በአንተም ላይ ከንፈሩን ቢከፍት! 6 የጥበቡን ኀይል ቢገልጥልህ! ባንተ ላይ ያለው እጥፍ ነውና። ያንጊዜም ከእግዚአብሔር ዘንድ በበደልህ ያገኘህ ትክክል እንደ ሆነ ታውቃለህ። 7 “የእግዚአብሔርን ፍለጋ ልትመረምር ትችላለህን? ወይስ ሁሉን የሚችል አምላክ ወደ ፈጠረው ፍጥረት ፍጻሜ ትደርሳለህን? 8 ሰማይ ከፍ ያለ ነው፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይልቅ የጠለቁ ነገሮች አሉ፤ ምን ታውቃለህ? 9 ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል። 10 እርሱ ሁሉን ቢገለብጥ፥ ምን አደረግህ? የሚለው ማን ነው? 11 እርሱ የኃጥኣን ሰዎች ሥራን ያውቃል፤ በደልንም ቢያይ ዝም ብሎ አይመለከትም፤ ይህንም አስተዋይ ሰው ያስተውላል። 12 ነገር ግን በከንቱ ነገርን የሚፈልግ ሰው፥ ከሴትም የሚወለድ ሟች የሜዳ አህያን ይመስላል። 13 አንተ ልብህን ንጹሕ ብታደርግ፥ እጆችህንም ወደ እርሱ ብትዘረጋ፥ 14 በእጆችህ በደል ቢኖር ካንተ አርቀው፤ በልብህም ኀጢአት አይኑር፤ 15 በዚያን ጊዜ ፊትህ በንጹሕ ውኃ እንደ ታጠበ ያበራል፥ መተዳደፍህንም ታስወግዳለህ፥ አትፈራምም። 16 መከራህንም እንዳለፈ ማዕበል ትረሳለህ፥ ከእንግዲህም ወዲያ አትደነግጥም። 17 ጸሎትህ እንደ አጥቢያ ኮከብ ይሆናል። ሕይወትህም እንደ ቀትር ብርሃን ያበራል። 18 ተስፋህንም ታገኝ ዘንድ ተዘልለህ ትቀመጣለህ፤ ያለ ኀዘንና ጭንቀትም በደኅንነት ትኖራለህ። 19 ታርፋለህ፥ የሚዋጋህም የለም፤ ብዙ ሰዎችም ይመጣሉ፤ ልመናም ያቀርቡልሃል። 20 የኃጥኣን መድኀኒታቸው ታልቃለች። ተስፋቸውንም ያጣሉ፥ የዝንጉዎች ዐይኖችም ይጠፋሉ።” |