ኢሳይያስ 66 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር በአሕዛብ ላይ እንደሚፈርድ 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድን ነው? 2 ይህ ሁሉ የእጄ ሥራ ነው፤ ይህም ሁሉ የእኔ ነው፥” ይላል እግዚአብሔር፤ “ወደ የዋሁና ወደ ጸጥተኛው፥ ከቃሌም የተነሣ ወደሚንቀጠቀጥ ሰው ከአልሆነ በቀር ወደ ማን እመለከታለሁ? 3 በሬን የሚሠዋልኝ ኃጥእ ውሻን እንደሚያርድልኝ ነው፤ የእህልን ቍርባን የሚያቀርብም የእሪያን ደም እንደሚያቀርብ ነው፤ ዕጣንንም ለመታሰቢያ የሚያጥን አምላክን እንደሚፀርፍ ነው፤ እነዚህ የገዛ መንገዳቸውን መረጡ፤ ነፍሳቸውም በርኵሰታቸው ደስ ይላታል። 4 እኔ ግን አዋርዳቸው ዘንድ፥ ስለ ኀጢአታቸውም እበቀላቸው ዘንድ እፈቅዳለሁ፤ እኔ በጠራሁ ጊዜ አልመለሱልኝምና፥ በተናገርሁም ጊዜ አልሰሙኝም፤ በፊቴም ክፉ ነገርን አደረጉ፤ ያልወደድሁትንም መረጡ።” 5 በቃሉ የምትንቀጠቀጡ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፥ “የእግዚአብሔር ስም ይከብር ዘንድ፦ ደስታችሁም ይገለጥ ዘንድ፥ እነርሱም ያፍሩ ዘንድ የሚጠሏችሁንና የሚጸየፉአችሁን ወንድሞቻችን በሏቸው። 6 የጩኸት ድምፅ ከከተማ፥ ድምፅም ከመቅደስ፥ በጠላቶቹም ላይ ፍዳን የሚያመጣ የእግዚአብሔር ድምፅ ተሰምቶአል። 7 “ሳታምጥ ወለደች፤ ምጥም ሳያገኛት ወንድ ልጅን ወለደች። 8 ከቶ እንዲህ ያለ ነገርን ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገርን ማን አይቶአል? በውኑ ሀገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን? ጽዮን እንዳማጠች ወዲያው ልጆችዋን ወልዳለችና። 9 እኔ ተስፋን ሰጠሁሽ፤ አንቺ ግን አላሰብሽኝም ይላል እግዚአብሔር። ሴት እንድትወልድ፥ መካንም እንዳትሆን የማደርግ እኔ አይደለሁምን?” ይላል አምላክሽ። 10 ኢየሩሳሌም ሆይ ደስ ይበልሽ፤ እርስዋንም የምትወድዱአት ሁሉ፥ በአንድነት ሐሤት አድርጉ፤ ስለ እርስዋም ያለቀሳችሁ ሁሉ፥ ከእርስዋ ጋር ደስ ይበላችሁ፤ 11 ትጠቡ ዘንድ ከማጽናናቷም ጡት ትጠግቡ ዘንድ እጅግ ጠጥታችሁ በክብርዋ ሙላት ደስ ይላችሁ ዘንድ። 12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “እነሆ፥ ሰላምን እንደ ወንዝ፥ የአሕዛብንም ክብር እንደሚጐርፍ ፈሳሽ እመልስላታለሁ፤ ልጆቻቸውንም በጫንቃቸው ላይ ይሸከሙአቸዋል፤ በጕልበታቸውም ላይ እያስቀመጡ ያቀማጥሏቸዋል። 13 እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ትጽናናላችሁ። 14 ታያላችሁ፤ ልባችሁም ሐሤት ታደርጋለች፤ አጥንታችሁም እንደ ለምለም ሣር ትበቅላለች፤ የእግዚአብሔርም እጅ ለሚፈሩት ትታወቃለች፤ ዐላውያንንም ያጠፋቸዋል።” 15 እነሆ፥ እግዚአብሔር መዓቱን በቍጣ፥ ዘለፋውንም በእሳት ነበልባል ይመልስ ዘንድ እንደ እሳት ይመጣል፤ ሰረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይሆናሉ። 16 ምድርም ሁሉ በእግዚአብሔር እሳት ሰውም ሁሉ በሰይፉ ይፈረድባቸዋል፤ በእግዚአብሔርም ተቀሥፈው የሞቱት ይበዛሉ። 17 “በአትክልት ቦታ ውስጥ ሰውነታቸውን የሚያጠሩና የሚያነጹ፥ በምግብ ቦታም የእሪያን ሥጋ፥ አስጸያፊ ነገርንም አይጥንም የሚበሉ በአንድነት ይጠፋሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 18 “ሥራቸውንና አሳባቸውን ዐውቄአለሁ፤ እነሆም እኔ እመጣለሁ፤ አሕዛብንና ልሳናትንም ሁሉ እሰበስባለሁ፤ እነርሱም ይመጣሉ፤ ክብሬንም ያያሉ። 19 በመካከላቸውም ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም ከሞት የዳኑትን ዝናዬን ወዳልሰሙ፥ ክብሬንም ወዳላዩ ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፥ ወደ ፉጥ፥ ወደ ሉድ፥ ወደ ሞሳሕ፥ ወደ ቶቤል፥ ወደ ኤላድ በሩቅ ወዳሉ ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በአሕዛብም መካከል ክብሬን ይናገራሉ። 20 የእስራኤል ልጆች ቍርባናቸውን በምስጋና ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደሚያመጡ፥ እንዲሁ ለእግዚአብሔር ቍርባን ይሆን ዘንድ ወንድሞቻችሁን ሁሉ፥ በፈረሶችና በሰረገሎች፥ በአልጋዎችና በበቅሎዎች፥ በጠያር ግመሎችም ላይ አድርገው፥ ከአሕዛብ ሁሉ ወደ ተቀደሰችው ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም ያመጡአቸዋል፥ ይላል እግዚአብሔር። 21 ካህናትና ሌዋውያን እንዲሆኑ ከእነርሱ እወስዳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 22 “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፥ እንዲሁ ዘራችሁና ስማችሁ ጸንተው ይኖራሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 23 እንዲህም ይሆናል፦ በየመባቻውና በየሰንበቱ ሥጋ ለባሽ ሁሉ በኢየሩሳሌም በፊቴ ይሰግድ ዘንድ ዘወትር ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 24 ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ፤ ትላቸው አይሞትም፤ እሳታቸውም አይጠፋም፤ ለሥጋ ለባሽም ሁሉ ምሳሌ ይሆናሉ።” |