ኢሳይያስ 58 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ እውነተኛ ጾም 1 በኀይልህ ጩኽ፤ አትቈጥብ፤ ድምፅህን እንደ መለከት አንሣ፤ ለሕዝቤ ኀጢአታቸውን፥ ለያዕቆብ ቤትም በደላቸውን ንገር። 2 ነገር ግን ጽድቅን እንደሚያደርግ የአምላኩንም ፍርድ እንደማይተው ሕዝብ ዕለት ዕለት ይሹኛል፤ መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ። አሁንም እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፤ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ። 3 “ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅኸንም?” ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። 4 እነሆ፥ ለጠብና ለክርክር ትጾማላችሁ፤ ድሃውንም በጡጫ ትማታላችሁ፤ በምትጮኹበት ጊዜ ድምፃችሁ እንዲሰማ ለእኔ ትጾማላችሁን? ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም። 5 እኔ ይህን ጾም የመረጥሁ አይደለሁም፤ እንደዚችም ባለች ቀን ሰው ራሱን ቢያሳዝን፥ አንገቱንም እንደ ቀለበት ቢያቀጥን፥ ማቅ ለብሶ በአመድ ላይ ቢተኛም፥ ይህ ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠ አይደለም። 6 ይህን ጾም የመረጥሁ አይደለም ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን የበደልን እስራት ፍታ፤ ጠማማውን ሁሉ አቅና፤ የተጨነቀውንም ሁሉ አድን፤ የዐመፃ ደብዳቤንም ተው። 7 ለተራበውም እንጀራህን አጥግበው፤ ድሆችን ወደ ቤትህ አስገብተህ አሳድራቸው፤ የተራቈተውንም ብታይ አልብሰው፤ ከሥጋ ዘመድህ አትሸሽግ። 8 ያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፤ ፈውስህም ፈጥኖ ይወጣል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይጋርድሃል። 9 ያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ፤ እርሱም፦ እነሆኝ፥ ይልሃል። የዐመፅ እስራትን ከመካከልህ ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ማንጐራጐርንም ብትተው፥ 10 ከምግብህም ለተራበ ብታካፍል፥ የተራበች ሰውነትንም ብታጠግብ፥ ያንጊዜ ብርሃንህ በጨለማ ይወጣል፤ ጨለማህም እንደ ቀትር ይሆናል። 11 እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ከአንተ ጋር ይኖራል፤ እንደ ነፍስህም ፍላጎት ያጠግብሃል፤ አጥንትህንም ያለመልማል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ። 12 ከድሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎችህ ይሠራሉ፤ መሠረትህም ለልጅ ልጅ ዘመን ይሆናል፤ አንተም፦ ሰባራውን ጠጋኝ፥ የመኖሪያ መንገድንም አዳሽ ትባላለህ። 13 ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፥ ሰንበትንም ደስታ፥ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ብታደርገው፥ ክፉ ሥራን ለመሥራት እግርህን ባታነሣ፥ በአፍህም ክፉ ነገርን ባትናገር፥ 14 በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ትታመናለህ፤ በምድርም በረከት ላይ ያወጣሃል፤ የአባትህ የያዕቆብንም ርስት ይመግብሃል፤ የእግዚአብሔር አፍ እንደዚህ ተናግሮአልና። |