ሕዝቅኤል 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የኢየሩሳሌም መቀጣት 1 እርሱም፥ “እያንዳንዳቸው የሚያጠፉባት መሣሪያን በእጃቸው ይዘው ከተማዪቱን የሚቀሥፉ ይቅረቡ” ብሎ በታላቅ ድምፅ በጆሮዬ ጮኸ። 2 እነሆም እያንዳንዳቸው ገጀሞ መሣሪያ በእጃቸው ይዘው ስድስት ሰዎች ወደ ሰሜን ከሚመለከተው ከላይኛው በር መንገድ መጡ፤ በመካከላቸውም የበፍታ ልብስ የለበሰና የሰንፔር መታጠቂያ በወገቡ የታጠቀ አንድ ሰው ነበረ። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ። 3 የእስራኤልም አምላክ ክብር በበላዩ ከነበረበት ኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤቱ መድረክ ሄዶ ነበር፤ በፍታም የለበሰውን፥ የሰንፔር መታጠቂያም በወገቡ የታጠቀውን ሰው ጠራ። 4 እግዚአብሔርም፥ “በከተማዪቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ፥ በመካከልዋም ስለ ተሠራው ኀጢአት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግንባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው። 5 እኔም እየሰማሁ ለሌሎቹ፦ በስተኋላው ወደ ከተማው ግቡ፤ ግደሉም፤ ዐይናችሁ አይራራ፤ ይቅርም አትበሉ፤ 6 ሽማግሌውንና ጎበዙን፥ ድንግሊቱንም፥ ሕፃናቱንና ሴቶቹን፥ ፈጽማችሁ ግደሉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ወደ አለበት ሰው ሁሉ አትቅረቡ፤ በመቅደሴም ጀምሩ” አላቸው። በቤቱም አንጻር ባሉ ሽማግሌዎች ጀመሩ። 7 እርሱም፥ “ቤቱን አርክሱ፤ ወጥታችሁ ግደሉ፤ በሙታንም መንገዶችን ሙሉ” አላቸው። 8 ሲገድሉም እኔ ብቻዬን ቀርቼ ሳለሁ በግንባሬ ተደፍቼ፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! ወዮ! መዓትህን በኢየሩሳሌም ላይ ስታፈስስ የእስራኤልን ቅሬታ ሁሉ ታጠፋለህን?” ብዬ ጮኽሁ። 9 እርሱም፥ “የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኀጢአት እጅግ በዝቶአል፤ ምድሪቱም በብዙ አሕዛብ እንደ ተመላች ከተማዪቱም እንዲሁ ዓመፅንና ርኵሰትን ተሞልታለች፤ እነርሱም፦ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል፤ እግዚአብሔርም አያይም” ብለዋል። 10 “እኔም ደግሞ በዐይኔ አልራራም፤ ይቅርታም አላደርግም፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ” አለኝ። 11 እነሆም በፍታ የለበሰው፥ የሰንፔር መታጠቂያም በወገቡ የታጠቀው ሰው መጣ፥ “ያዘዝኸኝንም አድርጌአለሁ” ብሎ በቃሉ መለሰ። |