ሕዝቅኤል 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል ፍጻሜ መቃረብ 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል፦ ፍጻሜ በእስራኤል ምድር ላይ መጣ፤ በምድሪቱ በአራቱም ማዕዘን ፍጻሜ መጣ። 3 አሁንም ፍጻሜ በአንቺ ላይ ደርሶአል። ቍጣዬንም እሰድድብሻለሁ፤ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፤ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። 4 ዐይኔም አይራራልሽም፤ እኔም ይቅር አልልሽም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ፤ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ነው፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” 5 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ክፋት በክፋት ላይ፤ እነሆ ይመጣል። 6 ፍጻሜ መጥቶአል፤ ፍጻሜ መጥቶአል፤ ነቅቶብሻል፤ እነሆ ደርሶአል። 7 በሀገር የምትኖር ሆይ! ስብራትህ ጊዜው ደረሰ፤ ቀኑም ቀረበ፤ የሽብር ቀን ነው እንጂ የተራራ ላይ ዕልልታ አይደለም፤ 8 አሁን በቅርብ መዓቴን አፈስስብሻለሁ፤ ቍጣዬንም እፈጽምብሻለሁ፤ እንደመንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፤ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ። 9 ዐይኔም አይራራም፤ እኔም ይቅር አልልም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ፤ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ነው፤ እኔም እግዚአብሔር የምቀሥፍ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 10 “እነሆ ቀኑ ደርሶአል፤ እነሆ! የእግዚአብሔር ቀን ወጥታለች፤ ስብራትህ ደርሶአል፤ ብትርም አብባለች፤ ስድብም በዝቶአል። 11 የኀጢአተኛው ምርኩዝ ተሰበረ፤ በደል በዛች፤ ይኸውም በሁከት አይደለም፤ በችኮላም አይደለም። 12 ጊዜው መጥቶአል፤ ቀኑ እነሆ ቀርቦአል፤ መቅሠፍቷ በሁለንተናዋ መልቶአልና የሚገዛ ደስ አይበለው፤ የሚሸጥም አይዘን። 13 የገዛው ወደ ሻጩ አይመለስም፤ ዳግመኛም በሕይወት ይኖራል፤ ሁለንተናዋን አይቶአልና አልተመለሰም፤ የሰው ሕይወቱ በዐይኑ ፊት ነው። 14 “መለከቱን ንፉ፤ ሁሉንም አዘጋጁ፤ ነገር ግን መዓቴ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና ወደ ሰልፍ የሚሄድ የለም። 15 ሰይፍ በውጭ፥ ቸነፈርና ራብ በውስጥ አለ፤ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፤ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይፈጁታል። 16 ከእነርሱም የሚሸሹ ይድናሉ፤ መብረርን እንደሚማር ርግብም በተራራ ላይ ይሆናሉ፤ እኔም በኀጢአታቸው ሁሉ እገድላለሁ። 17 እጅ ሁሉ ትደክማለች፤ ጕልበትም ሁሉ እንደ ውኃ ይሆናል። 18 ማቅም ትታጠቃላችሁ፤ ድንጋጤም ይሸፍናችኋል፤ በፊትም ሁሉ ላይ ሐፍረት ይሆናል፤ በራሳችሁም ሁሉ ላይ ቡሃነት ይሆናል። 19 ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ፤ ወርቃቸውም ይረክሳል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው አያድናቸውም። እርሱ የኀጢአታቸው እንቅፋት ሆኖአልና ሰውነታቸውን አያጠግቡም፤ ሆዳቸውንም አይሞሉም። 20 የክብሩንም ጌጥ ወደ ትዕቢት ለወጡ፤ የርኵስነታቸውንም ምስሎች አደረጉባት፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ አድርጌአታለሁ። 21 በባዕድም እጅ ለንጥቂያ፥ በምድር ኀጢአተኞችም እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እነርሱም ያረክሱአቸዋል። 22 ፊቴን ከእነርሱ እመልሳለሁ፤ ሥርዐቴንም ያረክሳሉ፤ ኀይለኞች ይገቡባታል፤ ያረክሱአትማል። 23 “ምድር በአሕዛብ እንደ ተመላች፥ ከተማም በኀጢአት ተመልታለችና ሰንሰለት ሥራ። 24 ከአሕዛብ ዘንድ ከሁሉ የሚከፉትን አመጣለሁ፤ ቤታቸውንም ይወርሳሉ፥ የኀያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፤ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ። 25 ጥፋት መጥቶአል፤ ሰላምም ይሻሉ፤ እርሱም አይገኝም። 26 ድንጋጤ በድንጋጤ ላይ ይመጣል፤ ወዮታ በወዮታ ላይ ይከተላል፤ ከነቢዩም ዘንድ ራእይን ይሻሉ፤ ከካህኑም ዘንድ ሕግ፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ ምክር ይጠፋል። 27 ንጉሡም ያለቅሳል፥ አለቃም ውርደትን ይለብሳል፤ የምድርም ሕዝብ እጅ ትሰላለች፤ እንደ መንገዳቸውም መጠን አደርግባቸዋለሁ፤ በፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” |