ሕዝቅኤል 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)እግዚአብሔር አምልኮ ጣዖትን እንደ ከለከለ 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አቅና፤ ትንቢትም ተናገርባቸው። 3 ለእስራኤል ተራሮች የጌታን የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በላቸው፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኮረብቶች፥ ለምንጮችና ለሸለቆዎች እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ የኮረብታ መስገጃዎቻችሁንም አጠፋለሁ። 4 መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፤ የፀሐይ ምስሎቻችሁም ይሰበራሉ፤ የተገደሉ ሰዎቻችሁንም በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ። 5 የእስራኤልንም ልጆች ሬሳዎች በጣዖቶቻቸው ፊት አኖራለሁ፤ አጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ። 6 በምትኖሩባትም ስፍራ ሁሉ ከተሞች ይፈርሳሉ፥ የኮረብታ መስገጃዎችም ሁሉ ውድማ ይሆናሉ፤ መሠዊያዎቻችሁም ይፈርሳሉ፤ ባድማም ይሆናሉ፤ ጣዖቶቻችሁም ይሰበራሉ፤ ያልቃሉም፤ የፀሐይ ምስሎቻችሁም ይጠፋሉ፤ ሥራችሁም ይሻራል። 7 ሙታኖቻችሁም በመካከላችሁ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 8 “ነገር ግን በሀገሮች በተበተናችሁ ጊዜ ከእናንተ ከአሕዛብ ጦር የዳኑትን አስቀራለሁ። 9 በዚያ በተማረኩበት በአሕዛብ ዘንድ ከእናንተ የዳኑት ያስቡኛል፤ ለሰሰኑበት፥ ከእኔም ለራቁበት ለልቡናቸው፥ ለሰሰኑ፥ ጣዖትንም ለተከተሉ ለዓይኖቻቸው ማልሁ፤ ጣዖቶቻቸውን ሁሉ እንዳመለኩ መጠን ስለ ሥራቸው ክፋት ፊታቸውን ይነጫሉ። 10 እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ ይህን ክፉ ነገር አደርግባቸው ዘንድ መናገሬ ለከንቱ አይደለም። 11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእጅህ አጨብጭብ፤ በእግርህም አሸብሽብ፤ ስለ እስራኤል ቤት ርኵሰት ሁሉ ወዮ ወዮ በል፤ በረኀብና በጦር፥ በቸነፈርም ይጠፋሉ። 12 በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፤ በቅርብም ያለው በሰይፍ ይወድቃል፤ በሀገር የቀረውና የተከበበውም በራብ ይሞታል፤ እንዲሁ መዓቴን እፈጽምባቸዋለሁ። 13 ሬሳዎቻቸው በጣዖቶቻቸው መካከልና በመሠዊያዎቻቸው ዙሪያ በወደቁ ጊዜ በረዣዥም ኮረብታ ሁሉ፥ በተራሮችም ራሶች ሁሉ፥ በዕንጨቱም ጥላ ሥር ለጣዖቶቻቸው ሁሉ፥ መልካም መዓዛን ባጠኑበት ከቅጠሉ ሁሉ በታች ሬሳዎቻቸው በወደቁ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 14 እጄንም እዘረጋባቸዋለሁ፤ በሚኖሩበትም ስፍራ ሁሉ ምድሪቱን ከዴብላታ ምድረ በዳ ይልቅ ውድማና በረሃ አደርጋታለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” |