ሕዝቅኤል 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሕዝቅኤል ምልክት ሊሆን ጠጕሩን መላጨቱ 1 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ራስን ከሚላጭ ምላጭ ይልቅ የተሳለ ጐራዴን ውሰድ፤ ወስደህም በእርስዋ ራስህንና ጢምህን ተላጭ፤ ሚዛንንም ውሰድ፤ ጠጕሩንም ትከፋፍለዋለህ። 2 የእስራትህም ወራት በተፈጸመ ጊዜ በከተማዪቱ መካከል ሢሶውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ሢሶውንም ወስደህ ዙሪያውን በጎራዴ ትመታለህ፤ ሢሶውንም ወደ ነፋስ ትበትናለህ፤ እኔም በኋላቸው ጎራዴ እመዝዛለሁ። 3 ከዚያም በቍጥር ጥቂቶቹን ውሰድ፤ በመጐናጸፊያህም ቋጥራቸው። 4 ከእነርሱም ደግሞ ወስደህ በእሳት ውስጥ ትጥላለህ፤ በእሳትም ታቃጥላቸዋለህ፤ ከእርስዋም እሳት ይወጣል፤ የእስራኤልንም ቤት ሁሉ እንዲህ ትላቸዋለህ።” 5 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህች ኢየሩሳሌም ናት፤ እርስዋንና አውራጃዎችዋንም በአሕዛብ መካከል አድርጌአለሁ፥ 6 እርስዋም ከአሕዛብ ይልቅ ፍርዴን በኀጢአት ለወጠች፤ በዙሪያዋም ከአሉ ሀገሮች ሁሉ ይልቅ ትእዛዜን ተላለፈች፤ ፍርዴን ጥለዋልና፥ በትእዛዜም አልሄዱምና። 7 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በዙሪያችሁ ላሉት አሕዛብ ሰበብ ሆናችኋልና፥ በትእዛዜም አልሄዳችሁምና፥ ፍርዴንም አልጠበቃችሁምና፥ በዙሪያችሁም እንደ አሉ እንደ አሕዛብ ፍርድ እንኳ አላደረጋችሁምና፥ 8 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ራሴ በአንቺ ላይ ነኝ፤ በአሕዛብም ፊት ፍርድን በመካከልሽ አደርጋለሁ። 9 ስለ ርኵሰትሽም ሁሉ ያልሠራሁትን፥ እርሱንም የሚመስል ደግሞ የማልሠራውን ነገር እሠራብሻለሁ። 10 ስለዚህ በመካከልሽ አባቶች ልጆቻቸውን ይበላሉ፤ ልጆችም አባቶቻቸውን ይበላሉ፤ ፍርድንም አደርግብሻለሁ፤ ከአንቺም የቀረውን ሁሉ ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ። 11 ስለዚህ እኔ ሕያው ነኝና በእድፍሽና በርኵሰትሽ መቅደሴን ስላረከስሽ፥ ስለዚህ በእውነት እኔ አሳንስሻለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ዐይኔም አይራራም፤ እኔም ይቅር አልልም። 12 ከአንቺም ሢሶው በቸነፈር ይሞታል፤ በመካከልሽም በራብ ያልቃል፤ ሢሶውም በዙሪያሽ በሰይፍ ይወድቃል፤ ሢሶውንም ወደ ነፋሳት ሁሉ እበትናለሁ፤ በኋላቸውም ሰይፍን እመዝዛለሁ። 13 “ቍጣዬንና መዓቴንም በእነርሱ ላይ እጨርሳለሁ፤ መዓቴንም በፈጸምሁባቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር በቅንዓቴ እንደ ተናገርሁ ታውቂያለሽ። 14 በዙሪያሽም በአሉ በአሕዛብ መካከል በሚያልፉም ሁሉ ፊት ከልጆችሽ ጋር አጠፋሻለሁ። 15 በቍጣዬና በመቅሠፍቴ በተበቀልሁሽ ጊዜ በዙሪያሽ በአሉ በአሕዛብ ዘንድ ትጨነቂያለሽ፤ ትደነግጫለሽም፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 16 ለማጥፋትም የሆነውን፥ አጠፋችሁም ዘንድ የምሰድደውን የራብ ፍላጻ በላያችሁ በሰደድሁ ጊዜ፥ ራብን እጨምርባችኋለሁ፤ የእንጀራችሁንም በትር እሰብራለሁ። 17 ራብንና ክፉዎችን አራዊት እሰድድብሻለሁ፤ እቀሥፍሻለሁ፤ ልጆችሽንም ያጠፋሉ ቸነፈርና ደምም በአንቺ ላይ ይመጡብሻል፤ ሰይፍንም አመጣብሻለሁ፤ ይከቡሻልም። እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” |