ሕዝቅኤል 48 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የምድሪቱ አከፋፈል 1 “የነገዶችም ስም ይህ ነው። በሔትሎን መንገድ አጠገብ ወደ ሐማት መግቢያ፥ በደማስቆም ድንበር በአለው በሐጸርዔናን በሐማትም አጠገብ በሰሜን በኩል ይጀምራል። ድንበራቸውም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ይሆናል። ለዳን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 2 ከዳንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለአሴር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 3 ከአሴርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለንፍታሌም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 4 ከንፍታሌም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለምናሴ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 5 ከምናሴም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለኤፍሬም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 6 ከኤፍሬምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለሮቤል አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 7 ከሮቤልም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሁዳ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 8 “ከይሁዳም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለመባ የተለየ ክፍል ይሆናል፤ ወርዱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ ርዝመቱም ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ከዕጣ ክፍሎች እንደ አንዱ ይሆናል፤ ቤተ መቅደሱም በመካከሉ ይሆናል። 9 ለእግዚአብሔር የምትለዩት መባ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። 10 የመቅደሱም ቀዳምያት ለካህናቱ ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ፥ በምዕራብም በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በምሥራቅም በኩል ወርዱ ዐሥር ሺህ፥ በደቡብም በኩል ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል። የእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ በመካከሉ ይሆናል። 11 የእስራኤልም ልጆች በሳቱ ጊዜ፥ ሌዋውያን እንደ ሳቱ ላልሳቱት፥ ሥርዐቴን ለጠበቁት፥ ከሳዶቅ ልጆች ወገን ለተቀደሱት ካህናት ይሆናል። 12 ከምድርም መባ የተለየ ሌላ መባ ይሆንላቸዋል፤ ከተቀደሱትም ይልቅ የተቀደሰ ይሆናል፤ በሌዋውያን ድንበር አጠገብ ይሆናል። 13 በካህናቱም ድንበር አቅራቢያ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ፥ ወርዱም ዐሥር ሺህ የሆነ ዕጣ ለሌዋውያን ይሆናል፤ ርዝመቱ ሁሉ ሃያ አምስት ሺህ፥ ወርዱም ሃያ ሺህ ክንድ ይሆናል። 14 ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ነውና ከእርሱ ምንም አይሸጡም፤ አይለውጡምም፤ የምድሩም ቀዳምያት አይፋለስም። 15 በሃያ አምስቱ ሺህ አንጻር አምስት ሺህ ወርድ ያለው የቀረ ቅዱስ ያይደለ ስፍራ ለከተማዪቱ ለጋራ ጉዳይዋ፥ ለመኖሪያ፥ ለማሰማርያም ይሆናል፤ ከተማዪቱም በመካከሉ ትሆናለች። 16 ልክዋም ይህ ነው፤ በሰሜን በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በደቡብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምሥራቅም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ፥ በምዕራብም በኩል አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል። 17 ለከተማዪቱም ማሰማርያ ይኖራታል፤ በሰሜን በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በደቡብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምሥራቅም በኩል ሁለት መቶ አምሳ፥ በምዕራብም በኩል ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል። 18 “በተቀደሰው መባ አንጻር የተረፈው ርዝመቱ ወደ ምሥራቅ ዐሥር ሺህ፥ ወደ ምዕራብም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። በተቀደሰው መባ አንጻር ይሆናል። ፍሬውም ከተማዪቱን ለሚያገለግሉ መብል ይሆናል። 19 ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ከተማዪቱን የሚያገለግሉ ያርሱታል። 20 መባው ሁሉ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ይሆናል፤ የተቀደሰውን መባ ከከተማዪቱ ይዞታ ጋር አራት ማዕዘን አድርጋችሁ ትሰጣላችሁ። 21 “በተቀደሰው መባና በከተማዪቱ ይዞታ፥ በዚህና በዚያ ወገን የቀረው ለአለቃው ይሆናል፤ በመባው በሃያ አምስት ሺህ ፊት እስከ ምሥራቁ ድንበር፥ በምዕራብም በኩል በሃያ አምስት ሺህ ፊት እስከ ምዕራቡ ድንበር፥ እንደ ዕጣ ክፍል ሁሉ መጠን፥ ለአለቃው ይሆናል፤ የተቀደሰውም መባና ቤተ መቅደሱ በመካከሉ ይሆናል። 22 የሌዋውያን ርስት፥ የከተማዪቱም ይዞታ ለአለቃው በሆነው መካከል ይሆናል፤ በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል የአለቃው ዕጣ ክፍል ይሆናል። 23 “ለቀሩትም ነገዶች እንዲህ ይሆናል፤ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለብንያም አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 24 ከብንያምም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለስምዖን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 25 ከስምዖንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለይሳኮር አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 26 ከይሳኮርም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለዛብሎን አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 27 ከዛብሎንም ድንበር ቀጥሎ ከምሥራቅ ጀምሮ እስከ ምዕራብ ድረስ ለጋድ አንድ የዕጣ ክፍል ይሆናል። 28 ከጋድም ድንበር ቀጥሎ በደቡብ በኩል ድንበሩ ከታማር ጀምሮ እስከ ሜሪባ ቃዴስ ውኃ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። 29 ርስት አድርጋችሁ ለእስራኤል ነገዶች በዕጣ የምታካፍሉአት ምድር ይህች ናት፤ የእያንዳንዱም ዕጣ እንደዚህ ነው፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የኢየሩሳሌም ቅጽር በሮች 30 “የከተማዪቱም መውጫዎች እነዚህ ናቸው። በሰሜን ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ነው። 31 የከተማዪቱ በሮች እንደ እስራኤል ነገዶች ስም ይሆናሉ፤ በሰሜን በኩል አንዱ የሮቤል በር፤ አንዱም የይሁዳ በር፥ አንዱም የሌዊ በር ሦስት በሮች ይሆናሉ። 32 በምሥራቁም ወገን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የዮሴፍ በር፥ አንዱም የብንያም በር፥ አንዱም የዳን በር ነው። 33 በደቡቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የስምዖን በር፥ አንዱም የይሳኮር በር፥ አንዱም የዛብሎን በር ነው። 34 በምዕራቡም ወገን ልኩ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፥ ሦስትም በሮች አሉ፤ አንዱ የጋድ በር፥ አንዱም የአሴር በር፥ አንዱም የንፍታሌም በር ነው። 35 ዙሪያዋም ዐሥራ ስምንት ሺህ ክንድ ይሆናል፥ ከዚያም ቀን ጀምሮ የከተማዪቱ ስም፦ ‘እግዚአብሔር በዚያ አለ’ ተብሎ ይጠራል።” |