ሕዝቅኤል 46 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል መስፍንና የበዓላት አከባበር 1 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በውስጠኛው አደባባይ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ሥራ በሚሠራበት በስድስቱ ቀን ተዘግቶ ይቈይ፤ ነገር ግን በሰንበት ቀን ይከፈት፤ በመባቻ ቀንም ይከፈት። 2 አለቃው በስተ ውጭ ባለው በር በደጀ ሰላሙ መንገድ ገብቶ በበሩ መቃን አጠገብ ይቁም፤ ካህናቱም የእርሱን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቅርቡ፥ እርሱም በበሩ መድረክ ላይ ይስገድ፤ ከዚያም በኋላ ይውጣ፤ በሩ ግን እስከ ማታ ድረስ አይዘጋ። 3 የሀገርም ሕዝብ በዚያ በር መግቢያ በእግዚአብሔር ፊት በሰንበታትና በመባቻ ይስገዱ። 4 አለቃውም በሰንበት ቀን ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸው ስድስት የበግ ጠቦቶች፥ ነውርም የሌለበት አንድ አውራ በግ ይሁን፤ 5 የእህሉም ቍርባን ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሁን፤ ለጠቦቶቹም የእህል ቍርባን እጁ እንደ ቻለ ያህል ይሁን፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ያቅርብ። 6 በመባቻም ቀን ነውር የሌለበትን አንድ ወይፈን፥ ነውር የሌለባቸውንም ስድስት ጠቦቶችና አንድ አውራ በግ ያቅርብ፤ 7 ለወይፈኑም አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአውራውም በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለጠቦቶቹም እጁ እንደ ቻለው ያህል፥ ለአንዱም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ለእህሉ ቍርባን ያቅርብ። 8 አለቃውም በሚገባበት ጊዜ በበሩ ደጀ ሰላም መንገድ ይግባ፤ በዚያውም ይውጣ። 9 “የሀገሩ ሕዝብ ግን በየክብረ በዓሉ ቀን ወደ እግዚአብሔር ፊት በመጡ ጊዜ በሰሜን በር በኩል ሊሰግድ የሚገባው በደቡብ በር በኩል ይውጣ፤ በደቡብም በር የሚገባው በሰሜን በር በኩል ይውጣ፤ በፊት ለፊት ይውጣ እንጂ በገባበት በር አይመለስ። 10 ሕዝቡ በሚገቡበት ጊዜ አለቃው በመካከላቸው ይግባ፤ በሚወጡበትም ጊዜ ይውጣ። 11 በበዓላትና በክብረ በዓል ቀኖች የእህሉ ቍርባን ለወይፈኑ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአውራ በጉ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለጠቦቶቹም እጁ እንደሚችለው ያህል፥ ለአንድ የኢፍ መስፈሪያ ዱቄት አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ይሆናል። 12 አለቃውም በፈቃዱ የሚያቀርበውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ ወይም በፈቃዱ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበውን የደኅንነቱን መሥዋዕት በአቀረበ ጊዜ፥ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት፤ በሰንበትም ቀን እንደሚያደርግ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚያም በኋላ ይውጣ፤ ከወጣም በኋላ በሩ ይዘጋ። 13 “በየዕለቱም ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት የበግ ጠቦት ለእግዚአብሔር ታቀርባለህ፤ በየማለዳው ታቀርበዋለህ። 14 ከእርሱም ጋር የእህልን ቍርባን፥ በኢን መስፈሪያ ሢሶ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ ስድስተኛ እጅ የስንዴ ዱቄትን፤ በየማለዳው ታቀርባለህ፤ ይህ የሚደረግ ዘለዓለማዊ ሥርዐት ነው። 15 እንዲሁ ዘወትር ለሚቃጠለው መሥዋዕት ጠቦቱንና የእህሉን ቍርባን ዘይቱንም በየማለዳው ያቀርባሉ።” 16 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “አለቃው ከልጆቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ ለልጆቹ ይሁን፤ የርስት ይዞታ ይሆንላቸዋል። 17 ነገር ግን ከአገልጋዮቹ ለአንዱ ከርስቱ ስጦታ ቢሰጥ እስከ ነፃነት ዓመት ድረስ ለእርሱ ይሁን፥ ከዚያም በኋላ ለአለቃው ይመለስ፤ ርስቱ ግን ለልጆቹ ይሁን። 18 አለቃውም ሕዝቡን ከይዞታቸው ያወጣቸው ዘንድ ከርስታቸው በግድ አይወሰድ፤ ሕዝቤ ሁሉ ከየይዞታቸው እንዳይነቀሉ ከገዛ ይዞታው ለልጆቹ ርስትን ይስጥ።” 19 በበሩም አጠገብ በአለው መግቢያ ወደ ሰሜን ወደሚመለከተው ለካህናት ወደሚሆን ወደ ተቀደሰው ዕቃ ቤት አገባኝ፤ እነሆም በኋላው በባሕር በኩል አንድ ስፍራ ነበረ። 20 እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ካህናቱ ሕዝቡን ለመቀደስ ወደ ውጭው አደባባይ እንዳይወጡ የበደሉን መሥዋዕትና የኀጢአቱን መሥዋዕት የሚያበስሉበት፥ የእህሉንም ቍርባን የሚጋግሩበት ስፍራ ይህ ነው።” 21 በውጭው አደባባይ አወጣኝ፤ በአደባባይም ወዳለው ወደ አራቱ ማዕዘን አዞረኝ፤ እነሆም፥ በአደባባዩ ማዕዘን ሁሉ አደባባይ ነበረ። 22 በአደባባዩ በአራቱ ማዕዘን ርዝመቱ አርባ ክንድ፥ ወርዱም ሠላሳ ክንድ የሆነ የታጠረ አደባባይ ነበረ፤ በማዕዘኑ ላሉ ለእነዚህ ለአራቱ ስፍራዎች አንድ ልክ ነበራቸው። 23 በአራቱም ዙሪያ ሁሉ ግንብ ነበረ፥ በግንቡም ሥር በዙሪያው የመቀቀያ ቦታ ነበረ። 24 እርሱም፥ “እነዚህ የቤቱ አገልጋዮች የሕዝቡን መሥዋዕት የሚያበስሉባቸው ስፍራዎች ናቸው” አለኝ። |