ሕዝቅኤል 45 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የምድር ርስት አከፋፈል 1 “ርስትም አድርጋችሁ ምድርን በዕጣ በምታካፍሉበት ጊዜ ከምድር የተቀደሰውን የዕጣ ክፍል መባ አድርጋችሁ ወደ እግዚአብሔር ታቀርባላችሁ። ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ሺህ ክንድ ይሆናል፤ በዳርቻው ሁሉ ዙሪያው የተቀደሰ ይሆናል። 2 ከእርሱም ርዝመቱ አምስት መቶ፥ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ አራት ማዕዘን የሆነ ቦታ ለመቅደሱ ይሆናል፤ በዙሪያውም ባዶ ስፍራ የሚሆን አምሳ ክንድ ይሆናል። 3 ከዚያው ልክ ደግሞ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ፥ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ የሆነ ስፍራ ትለካለህ፤ በእርሱም ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳን የሆነ መቅደስ ይሆናል። 4 ከምድርም የተቀደሰ የዕጣ ክፍል ይሆናል፤ እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ለሚቀርቡ ለመቅደሱ አገልጋዮች ለካህናቱ ይሆናል፤ ለቤቶቻቸውም የሚሆን ስፍራ፥ ለመቅደስም የሚሆን የተቀደሰ ስፍራ ይሆናል። 5 ርዝመቱም ሃያ አምስት ሺህ፥ ወርዱም ዐሥር ሺህ የሆነ ስፍራ ለቤቱ አገልጋዮች ለሌዋውያን መኖሪያ ርስት ከሃያ ዕቃ ቤቶች ጋር ይሆናል። 6 “ለከተማዪቱም ይዞታ በተቀደሰው የዕጣ ክፍል መባ አጠገብ ወርዱ አምስት ሺህ፥ ርዝመቱም ሃያ አምስት ሺህ የሆነውን ስፍራ ታደርጋላችሁ። እርሱም ለእስራኤል ቤት ሁሉ ይሆናል። 7 ለአለቃውም የሆነ የዕጣ ክፍል በተቀደሰው መባና በከተማዪቱ ይዞታ አጠገብ በዚህና በዚያ ይሆናል፤ በተቀደሰው መባና በከተማዪቱ ይዞታ ፊት በምዕራብ በኩል ወደ ምዕራብ፥ በምሥራቅም በኩል ወደ ምሥራቅ ይሆናል፤ ርዝመቱም እንደ አንድ ነገድ ዕጣ ክፍል ሆኖ ከምድሩ ከምዕራቡ ዳርቻ ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ዳርቻ ድረስ ይሆናል። 8 ይህም በእስራኤል ዘንድ ይዞታ ይሆንለታል፤ የሕዝቤ አለቆችም ለእስራኤል ቤት ምድሪቱን እንደ ነገዳቸው መጠን ይሰጡአቸዋል እንጂ ሕዝቤን ከእንግዲህ ወዲህ አያስጨንቋቸውም።” 9 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእስራኤል አለቆች ሆይ! ይብቃችሁ፤ ግፍንና ዐመፅን አስወግዱ፤ ፍርድንና ጽድቅንም አድርጉ፤ ቅሚያችሁን ከሕዝቤ ላይ አርቁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 10 እውነተኛ ሚዛን፥ እውነተኛም የኢፍ መስፈሪያ፥ እውነተኛም የባዶስ መስፈሪያ ይሁንላችሁ። 11 እንዲሁም የኢፍና የባዶስ መስፈሪያ አንድ ይሁን፤ የባዶስ መስፈሪያ፥ የቆሮስ መስፈሪያ ዐሥረኛ ክፍል፥ የኢፍ መስፈሪያውም የቆሮስ መስፈሪያ ዐሥረኛ ክፍል ይሁን። መስፈሪያው እንደ ቆሮስ መስፈሪያ ይሁን። 12 ሰቅሉም ሃያ አቦሊ ይሁን፤ ሃያ ሰቅል፥ ሃያ አምስት ሰቅል፥ ዐሥራ አምስት ሰቅል፥ ምናን ይሁንላችሁ። 13 “የምታቀርቡት መባ ይህ ነው፤ ከአንድ ቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ፥ ከአንድም ቆሮስ መስፈሪያ ገብስ አንድ ስድስተኛ የኢፍ መስፈሪያ ትሰጣላችሁ። 14 የዘይቱም ደንብ፥ ከእያንዳንዱ የቆሮስ መስፈሪያ የባዶስን ዐሥረኛ ክፍል ትሰጣላችሁ፤ ዐሥር የባዶስ መስፈሪያ አንድ የቆሮስ መስፈሪያ ነውና። 15 ከእስራኤል ማሰማርያ ከመንጋው ከሁለት መቶው አንዱን የበግ ጠቦት ትሰጣላችሁ፤ ይህ ኀጢአታችሁን ያስተሰርይላችሁ ዘንድ ለእህል ቍርባንና ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለደኅንነትም መሥዋዕት ይሆናል” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16 የሀገሩም ሕዝብ ሁሉ ይህን መባ ለእስራኤል አለቃ ይሰጣሉ። 17 በየበዓላቱም፥ በየመባቻውም፥ በየሰንበታቱም በእስራኤልም ቤት ዓመት በዓል ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን፥ የመጠጡንም ቍርባን መስጠት በአለቃው ላይ ይሆናል፤ እርሱ ለእስራኤል ቤት ያስተሰርይ ዘንድ የኀጢአቱን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርባል።” 18 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ከመንጋው ነውር የሌለበትን ወይፈን ውሰድ፤ መቅደሱንም አንጻ። 19 ካህኑም ከኀጢአቱ መሥዋዕት ደም ወስዶ በመቅደሱ መቃኖችና በመሠዊያው እርከን በአራቱ ማዕዘን፥ በውስጠኛውም አደባባይ በበሩ መቃኖች ላይ ይርጨው። 20 ከወሩም በሰባተኛው ቀን እንዲሁ አድርግ፤ ይኸውም ስለ ሳተውና ስለ በደለው ሁሉ ነው። እንዲሁ ስለ ቤቱ አስተስርዩ። 21 “በመጀመሪያው ወር ከወሩም በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታደርጋላችሁ። እስከ ሰባት ቀንም ድረስ ቂጣ ትበላላችሁ። 22 በዚያም ቀን አለቃው ለራሱና ለሀገሩ ሕዝብ ሁሉ የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ያቅርብ። 23 በበዓሉም በሰባቱ ቀኖች የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ሰባቱን ቀኖች በየዕለቱ ነውር የሌለባቸውን ሰባት ወይፈንና ሰባት አውራ በጎች ያቅርብ፤ ለኀጢአትም መሥዋዕት በየዕለቱ ከፍየሎች አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ። 24 ለአንድም ወይፈን አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአንድም አውራ በግ አንድ የኢፍ መስፈሪያ፥ ለአንድም የኢፍ መስፈሪያ አንድ የኢን መስፈሪያ ዘይት ለእህል ቍርባን ያቅርብ። 25 በሰባተኛውም ወር ከወሩም በዐሥራ አምስተኛው ቀን በበዓሉ ሰባት ቀኖች፥ የኃጢአቱን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን ከዘይቱ ጋር እንዲሁ ያቅርብ።” |