ሕዝቅኤል 44 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የተዘጋችው የምሥራቅ በር 1 ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተ ውጭ ወደ አለው ወደ መቅደሱ በር መለሰኝ፤ ተዘግቶም ነበር። 2 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ይህች በር ተዘግታ ትኖራለች እንጂ አትከፈትም፤ ሰውም አይገባባትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶባታልና ተዘግታ ትኖራለች። 3 አለቃው ግን እርሱ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ይበላ ዘንድ ይቀመጥባታል፤ በበሩ ይገባል፤ በዚያም መንገድ ይወጣል።” 4 በሰሜኑም በር መንገድ በቤቱ ፊት አገባኝ፤ እኔም አየሁ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር የእግዚአብሔርን ቤት መልቶት ነበር፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ። 5 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ልብ አድርግ፤ ስለ እግዚአብሔርም ቤት ሥርዐትና ሕግ ሁሉ የምነግርህን ሁሉ በዐይንህ ተመልከት፤ በጆሮህም ስማ፤ የቤቱንም መግቢያ፥ የመቅደሱንም መውጫ ሁሉ ልብ አድርግ። 6 ለዐመፀኛው ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ! ርኵሰታችሁ ሁሉ ይብቃችሁ። 7 እንጀራዬን፥ ስብንና ደምን በምታቀርቡበት ጊዜ በመቅደሴ ውስጥ ይሆኑ ዘንድ ቤቴንም ያረክሱ ዘንድ፥ በልባቸውና በሥጋቸው ያልተገረዙትን እንግዶችን ሰዎች አግብታችኋልና፥ በርኵሰታችሁም ሁሉ ቃል ኪዳኔን አፍርሳችኋልና። 8 የመቅደሴን ሥርዐት አልጠበቃችሁም፤ ነገር ግን የመቅደሴን ሥርዐት የሚጠብቁ ሌሎችን ለራሳችሁ ሾማችሁ።” 9 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በእስራኤል ልጆች መካከል ከአሉት ሁሉ በልቡና በሥጋው ያልተገረዘ የባዕድ ልጅ እንግዳ ሁሉ ወደ መቅደሴ አይግባ። 10 ከእኔ ዘንድ የራቁ፥ እስራኤልም በሳቱ ጊዜ ጣዖታቸውን ተከትለው ከእኔ ዘንድ የሳቱ ሌዋውያን ሳይቀር ኀጢአታቸውን ይሸከማሉ። 11 ነገር ግን በመቅደሴ ውስጥ አገልጋዮች ይሆናሉ፤ በቤቱም በሮች በረኞች ይሆናሉ፤ በቤቱም ውስጥ ያገለግላሉ፤ ለሕዝቡም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትን ይሠዋሉ፤ ያገለግሉአቸውም ዘንድ በፊታቸው ይቆማሉ። 12 በጣዖቶቻቸውም ፊት አገልግለዋቸው ነበሩና፥ ለእስራኤልም ቤት የኀጢአት እንቅፋት ሆነዋልና ስለዚህ እጄን በላያቸው አንሥቻለሁ፤ ኀጢአታቸውንም ይሸከማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 13 እኔንም በክህነት ለማገልገል ወደ እኔ አይቀርቡም፤ ወደ ተቀደሰውም ነገሬና ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ነገር አይቀርቡም፤ እፍረታቸውንና የሠሩትንም ርኵሰታቸውን ይሸከማሉ። 14 ነገር ግን ለአገልግሎቱ ሁሉና በእርሱ ውስጥ ለሚደረገው ሁሉ የቤቱን ሥርዐት ጠባቂዎች አደርጋቸዋለሁ። 15 “ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ከእኔ ዘንድ በሳቱ ጊዜ የመቅደሴን ሥርዐት የጠበቁ የሳዶቅ ልጆች ሌዋውያን ካህናት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ይቀርባሉ፤ ስቡንና ደሙንም ወደ እኔ ያቀርቡ ዘንድ በፊቴ ይቆማሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16 ወደ መቅደሴም ይገባሉ፤ ያገለግሉኝም ዘንድ ወደ ገበታዬ ይቀርባሉ፤ ሥርዐቴንም ይጠብቃሉ። 17 ወደ ውስጠኛውም አደባባይ በር በገቡ ጊዜ የተልባ እግር ልብስ ይልበሱ፤ በውስጠኛውም አደባባይ በርና በቤቱ ውስጥ በአገለገሉ ጊዜ ከበግ ጠጕር አንዳች ነገር በላያቸው አይሁን። 18 በራሳቸው ላይ የተልባ እግር መጠምጠሚያ ይሁን፤ በወገባቸውም ላይ የተልባ እግር ሱሪ ይሁን፤ የሚያልብ ነገር አይታጠቁ። 19 ወደ ውጭውም አደባባይ ወደ ሕዝብ በወጡ ጊዜ ያገለገሉበትን ልብሳቸውን ያውልቁ፤ በተቀደሰውም ዕቃ ቤት ውስጥ ያኑሩት፤ ሕዝቡንም በልብሳቸው እንዳይቀድሱ ሌላውን ልብስ ይልበሱ። 20 ራሳቸውንም አይላጩ፥ የራሳቸውንም ጠጕር ይከርከሙ እንጂ ጠጕራቸውን አያሳድጉ። 21 ካህናቱም ሁሉ በውስጠኛው አደባባይ ሲገቡ የወይን ጠጅ አይጠጡ። 22 መበለቲቱንና የተፈታችይቱን አያግቡ፤ ከእስራኤል ቤት ዘር ግን ድንግሊቱን ወይም የካህን ሚስት የነበረችይቱን መበለት ያግቡ። 23 በተቀደሰውና ባልተቀደሰው መካከል ይለዩ ዘንድ ሕዝቤን ያስተምሩ፤ ንጹሕና ንጹሕ ባልሆነው መካከል ይለዩ ዘንድ ያሳዩአቸው። 24 ክርክርም በሆነ ጊዜ ለመፍረድ ይቁሙ፤ እንደ ፍርዴ ይፍረዱ፤ በበዓላቴ ሁሉ ሕጌንና ሥርዐቴን ይጠብቁ፤ ሰንበታቴንም ይቀድሱ። 25 እንዳይረክሱም ወደ ሞተ ሰው አይግቡ፤ ነገር ግን ለአባት፥ ወይም ለእናት፥ ወይም ለወንድ ልጅ፥ ወይም ለሴት ልጅ፥ ወይም ለወንድም፥ ወይም ላልተዳረች እኅት ይርከሱ። 26 ከነጻም በኋላ ሰባት ቀን ይቍጠሩለት። 27 በመቅደስም ውስጥ ያገለግል ዘንድ ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን የኀጢአትን መሥዋዕት ያቅርብ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 28 “ርስት አይሆንላቸውም፤ እኔ ርስታቸው ነኝ፤ በእስራኤልም ልጆች ዘንድ ርስት አትስጡአቸው፤ እኔ ርስታቸው ነኝ፤ 29 የእህሉን ቍርባንና የኀጢአትን መሥዋዕት የንስሓንም መሥዋዕት ይበላሉ፤ በእስራኤልም ዘንድ እርም የሆነው ነገር ሁሉ ለእነርሱ ይሆናል። 30 የበኵራቱ ሁሉ መጀመሪያ ከየዓይነቱ፥ ከቍርባናችሁም ሁሉ የማንሣት ቍርባን ሁሉ ለካህናት ይሆናል፤ በቤታችሁም ውስጥ በረከት ያድር ዘንድ የአዝመራችሁን ቀዳምያት ለካህናቱ ትሰጣላችሁ። 31 ከዎፍም ሆነ ከእንስሳ የበከተውንና አውሬ የሰበረውን ካህናት አይብሉት። |