ሕዝቅኤል 43 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን 1 ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በር አመጣኝ። 2 እነሆም የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፤ ከክብሩም የተነሣ ምድር ታበራ ነበር። 3 ያየሁትም ራእይ ከተማዪቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንደ አየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮቦር ወንዝ እንደአየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ። 4 የእግዚአብሔርም ክብር ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር ወደ መቅደሱ ገባ። 5 መንፈስም አነሣኝ፤ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፤ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር መቅደሱን መልቶት ነበር። 6 በመቅደሱም ሆኖ የሚናገረኝን ሰማሁ፤ በአጠገቤም ሰው ቆሞ ነበር። 7 እንዲህም አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘለዓለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ መረገጫ ይህ ነው። ዳግመኛም የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በዝሙታቸውና በከፍታዎቻቸው በአለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም። 8 መድረካቸውን በመድረኬ አጠገብ፥ መቃናቸውንም በመቃኔ አጠገብ አድርገዋልና። በእኔና በእነርሱ መካከል ግንብ ብቻ ነበረ፤ በሠሩትም ርኵሰት ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው። 9 አሁንም ዝሙታቸውንና የነገሥታቶቻቸውን ሬሳ ከእኔ ዘንድ ያርቁ፤ እኔም ለዘለዓለም በመካከላቸው አድራለሁ። 10 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ሥራቸውንና ኀጢአታቸውን ይተዉ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ይህን ቤት አሳያቸው፤ አምሳያውንም ይለኩ። 11 እነርሱም ስለ ሠሩት ሥራ ሁሉ መቅሠፍታቸውን ያገኛሉ፤ አንተም የቤቱን መልክና ምሳሌውን፥ መውጫውንም፥ መግቢያውንም፥ ሥርዐቱንም፥ ሕጉንም ሁሉ አስታውቃቸው፤ ሥርዐቱንና ሕጉን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ፥ ያደርጉትም ዘንድ በፊታቸው ጻፈው። 12 በተራራው ራስ ላይ ያለውን ቤቱንና የቤቱን ሥርዐት ሣል፤ የዙሪያውም ዳርቻ ሁሉ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። እነሆ የቤቱ ሕግ ይህ ነው።” የመሠውያ አሠራር 13 የመሠዊያው ልክ በክንድ ይህ ነው፤ ክንዱም ክንድ ተጋት ነው። የመሠረቱም ቁመቱ አንድ ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ አንድ ስንዝርም ክፈፍ ዳር ዳሩን በዙሪያው አለ፤ የመሠዊያው ቁመት እንዲሁ ነው። 14 በመሬቱም ላይ ከአለው መሠረት ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ ከትንሹም እርከን ጀምሮ እስከ ትልቁ እርከን ድረስ አራት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው። 15 ምድጃውም አራት ክንድ ነው፤ በምድጃውም ላይ አንድ ክንድ ወደ ላይ ከፍ የሚሉ አራት ቀንዶች አሉበት። 16 የምድጃውም ርዝመት ዐሥራ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው። 17 የእርከኑም ርዝመት ዐሥራ አራት ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ አራት ክንድ ነው፤ አራቱም መዐዝን ትክክል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ክፈፍ የክንድ እኩሌታ ነው፤ መሠረቱም በዙሪያው አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹም ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ።” 18 እንዲህም አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ፥ ደሙንም ይረጩበት ዘንድ በሚሠሩበት ቀን የመሠዊያው ሕግ ይህ ነው። 19 ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ከሳዶቅ ዘር ለሚሆኑ ለሌዋውያኑ ካህናት ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ከመንጋው አንድ ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 20 ከደሙም ትወስዳለህ፤ በአራቱ የመሠዊያ ቀንዶቹም፥ በእርከኑም በአራቱ ማዕዘን ላይ፥ በዙሪያውም በአለው ክፈፍ ላይ ትረጨዋለህ፤ እንዲሁ ታነጻዋለህ፤ ታስተሰርይለትማለህ። 21 ለኀጢአትም መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትወስዳለህ፤ በመቅደሱም ውጭ በቤቱ በተለየው ስፍራ ይቃጠላል። 22 በሁለተኛውም ቀን ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ነውር የሌለበትን አውራ ፍየል ታቀርባለህ፤ በወይፈኑም እንዳነጹት እንዲሁ መሠዊያውን ያነጹበታል። 23 ማንጻቱንም ከፈጸምህ በኋላ ነውር የሌለበትን ወይፈን፥ ከበጎችም ነውር የሌለበትን ጠቦት በግ ታቀርባለህ፤ 24 በእግዚአብሔርም ፊት ታቀርባቸዋለህ፤ ካህናቱም ጨው ይጨምሩባቸዋል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር ያቀርቡአቸዋል። 25 ሰባት ቀንም በየዕለቱ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ ፍየል ታቀርባለህ፤ ነውርም የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ከበጎችም አንድ ጠቦት በግ ያቀርባሉ። 26 ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሠርያሉ፤ ያነጹታል፤ ይቀድሱትማል። 27 ቀኖቹንም በፈጸሙ ጊዜ በስምንተኛው ቀን ከዚያም በኋላ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ የደኅንነት መሥዋዕታችሁንም በመሠዊያው ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |