ሕዝቅኤል 42 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በውጭም አደባባይ በሰሜኑ መንገድ በምሥራቅ በኩል አወጣኝ፤ በልዩውም ስፍራ አንጻርና በሰሜን በኩል በአለው ግቢ ፊት ለፊት ወዳሉት አምስት ዕቃ ቤቶች አገባኝ። 2 መቶ ክንድ በሆነው ርዝመት ፊት በሰሜን በኩል መዝጊያ ነበረ፤ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበረ። 3 በውስጠኛውም አደባባይ በሃያው ክንድ አንጻር፥ በውጭውም አደባባይ በወለሉ አንጻር በሦስት ደርብ በትይዩ የተሠራ መተላለፊያ ነበረ። 4 በዕቃ ቤቶቹም ፊት በስተውስጥ ወርዱ ዐሥር ክንድ፥ ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ መንገድ ነበረ፤ መግቢያዎቻቸውም ወደ ሰሜን ይመለከቱ ነበር። 5 መተላለፊያውም አሳጥሮአቸዋልና ላይኞቹ ዕቃ ቤቶች ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ አጫጭር ነበሩ። 6 በሦስትም ደርብ ተሠርተው ነበርና፥ በአደባባዩም እንዳሉት አዕማድ፥ አዕማድ አልነበሩላቸውምና ስለዚህ ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ ጠባብ ነበሩ። 7 በውጭ በዕቃ ቤቶቹ አጠገብ ያለው፥ ወደ ውጭው አደባባይ የሚያመለክተው ቅጥር፥ በዕቃ ቤቶች ትይዩ የሆነ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ነበረ። 8 በመቅደሱ ፊት የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው መቶ ክንድ ሲሆን፥ በውጭው አደባባይ በኩል የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው አምሳ ክንድ ነበረና። 9 ከእነዚህም ዕቃ ቤቶች በታች በስተምሥራቅ በኩል፥ ሰው ከውጭው አደባባይ የሚገባበት መግቢያ ነበረ፤ ይህም በቅጥሩ ራስ አጠገብ ነበረ። 10 በደቡብም በኩል በልዩው ስፍራና በግቢው አንጻር ዕቃ ቤቶች ነበሩ። 11 በስተፊታቸውም የነበረ መንገድ በሰሜን በኩል እንደ ነበረው እንደ ዕቃ ቤቶቹ መንገድ አምሳል ነበር። ርዝመታቸውም፥ ወርዳቸውም፥ መውጫቸውም፥ ሥርዐታቸውም፥ መዝጊያዎቻቸውም በዚያው ልክ ነበሩ። 12 በደቡብም በኩል ከአሉት ዕቃ ቤቶች በታች በምሥራቅ በኩል በቅጥሩ ራስ አጠገብ መግቢያ በር ነበር። 13 እንዲህም አለኝ፥ “በልዩ ስፍራ አንጻር በሰሜንና በደቡብ በኩል ያሉ ዕቃ ቤቶች፥ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ካህናቱ ከሁሉ ይልቅ የተቀደሰውን ምግብ የሚበሉባቸው ቤቶች ናቸው። ስፍራው ቅዱስ ነውና በዚያ የተቀደሰውን ነገር፥ የእህሉን ቍርባን፥ የኀጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕት ያኖራሉ። 14 ካህናቱም በገቡ ጊዜ ከመቅደሱ በውጭው አደባባይ አይወጡም፤ የሚያገለግሉበትን ልብሳቸውን ግን ቅዱስ ነውና በዚያ ያኖሩታል፤ ሌላም ልብስ ለብሰው ወደ ሕዝብ ይወጣሉ።” 15 ውስጠኛውንም ቤት ለክቶ በፈጸመ ጊዜ ወደ ምሥራቅ በሚመለከተው በር መንገድ አወጣኝ፤ እርሱንም ዙሪያውን ለካው። 16 ወደ ምሥራቅ በሚመለከተውም በር ኋላ ቆመ፤ የምሥራቁን ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 17 ወደ ሰሜንም ዞረ፤ የሰሜኑንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 18 ወደ ደቡብም ዞረ፤ የደቡቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 19 ወደ ምዕራብም ዞረ፤ የምዕራቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 20 በአራቱም ወገን ለካ፤ የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን ይለይ ዘንድ ርዝመቱ አምስት መቶ ክንድ፥ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ የሆነ ቅጥር በዙሪያው ነበረ። |