ሕዝቅኤል 40 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ አዲሱ ቤተ መቅደስ የተገለጠ ራእይ 1 በተማረክን በሃያ አምስተኛው ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ከወሩ በዐሥረኛው ቀን፥ ከተማዪቱ ከተመታች በኋላ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረ፤ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ። 2 በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ፤ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፤ በዚያም ላይ እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር በፊቴ ነበረ። 3 ወደዚያም አመጣኝ፤ እነሆም መልኩ እንደሚያንፀባርቅ ናስ መልክ የመሰለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፤ በእጁም የተልባ እግር ገመድና የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ እርሱም በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር። 4 ያም ሰው፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን አሳይህ ዘንድ አንተ ወደዚህ መጥተሃልና በዐይንህ እይ፤ በጆሮህም ስማ፤ የማሳይህንም ሁሉ በልብህ ጠብቅ፤ የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር” አለኝ። 5 እነሆም በቤቱ ውጭ በዙሪያው ቅጥር ነበረ፤ በሰውየውም እጅ የክንዱ ልክ አንድ ክንድ ከጋት የሆነ ስድስት ክንድ ያለበት የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ የቅጥሩንም ስፋት አንድ ዘንግ ቁመቱንም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ። 6 ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተውም በር መጣ፤ በሰባቱም ደረጃዎች ላይ ወጣ፤ በበሩ በኩል ያለውንም የመድረኩን ወለል ወርዱን አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ፤ የሁለተኛውም ወለል ወርድ አንድ ዘንግ ነበረ። 7 የዕቃ ቤቱ ሁሉ ርዝመት አንድ ዘንግ፤ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበረ፤ በዕቃ ቤቶቹም መካከል አምስት ክንድ ነበረ፤ በበሩም ደጀ ሰላም፤ በስተውስጥ በኩል የሚገኝ የበሩ የመድረክ ወለል አንድ ዘንግ ነበረ። 8 በስተውስጥም ያለውን የበሩን ደጀሰላም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ። 9 የበሩንም ደጀ ሰላም ስምንት ክንድ፤ የግንቡንም አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ደጀ ሰላም በስተውስጥ ነበረ። 10 የምሥራቁም ዕቃ ቤቶች በዚህ በኩል ሦስት፥ በዚያም በኩል ሦስት፥ ነበሩ፤ ለሦስቱም አንድ ልክ ነበረ፤ የግንቡም አዕማድ ወርድ በዚህ በኩልና በዚያ በኩል አንድ ልክ ነበረ። 11 የበሩንም መግቢያ ወርድ ዐሥር ክንድ፥ የበሩንም ርዝመት ዐሥራ ሦስት ክንድ አድርጎ ለካ። 12 በዕቃ ቤቱም ፊት በዚህ በኩል አንድ ክንድ፥ በዚያም በኩል አንድ ክንድ የሆነ ዳርቻ ነበረ፤ የዕቃ ቤቱም በዚህ በኩል ስድስት ክንድ በዚያም በኩል ስድስት ክንድ ነበሩ። 13 ከአንዱም የዕቃ ቤት ደርብ ጀምሮ እስከ ሌላው ደርብ ድረስ የበሩን ወርድ ሃያ አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ በሩና በሩም ትይዩ ነበረ። 14 ደጀ ሰላሙንም ሃያ ክንድ አድርጎ ለካ፤ በበሩም ደጀ ሰላም ዙሪያ አደባባይ ነበረ። 15 ከበሩም መግቢያ ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው የበሩ ደጀ ሰላም መጨረሻ ድረስ አምሳ ክንድ ነበረ። 16 በዕቃ ቤቶቹም በበሩ ውስጥ በዙሪያው በነበሩትም በግንቡ አዕማድ የዐይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩባቸው፤ ደግሞም በደጀ ሰላሙ ውስጥ በዙሪያው መስኮቶች ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ሁሉ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር። 17 ወደ ውስጠኛው አደባባይም አገባኝ፤ እነሆም በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ዕቃ ቤቶችና ወለል ነበሩ፤ በወለሉም ላይ ሠላሳ ዕቃ ቤቶች ነበሩ። 18 ወለሉም በበሮች አጠገብ ነበረ፤ ይህም ታችኛው ወለል እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበረ። 19 ከታችኛውም በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ወርዱን አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ወደ ምሥራቅና ወደ ሰሜን ለካ። 20 ወደ ሰሜንም መራኝ፤ እነሆም በውጭው አደባባይ ያለ ወደ ሰሜን የሚመለከት በር ነበረ፤ ርዝመቱንና ወርዱንም ለካ። 21 የዕቃ ቤቶቹም በዚህ በኩል ሦስት፥ በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፤ የግንቡ አዕማድና መዛነቢያዎቹም፥ ወደ ምሥራቅ የሚያሳዩ ዘንባባዎቹም አምሳ ክንድ ነበሩ፤ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 22 መስኮቶቹም፥ መዛነቢያዎቹም፥ የዘንባባ ዛፎቹም ወደ ምሥራቅ እንደሚመለከተው በር ልክ ነበሩ፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ። 23 በውስጠኛውም አደባባይ በሰሜኑና በምሥራቁ በኩል በሌላው በር አንጻር በር ነበረ፤ ከበርም እስከ በር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 24 ወደ ደቡብም መራኝ፤ እነሆም ወደ ደቡብ የሚመለከት በር ነበረ፤ የግንቡን አዕማድና መዛነቢያዎቹንም እንደዚያው መጠን አድርጎ ለካ። 25 በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ እንደ እነዚያ መስኮቶች የሚመስሉ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 26 ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ላይ አንዱ በዚህ አንዱም በዚያ ወገን ሆኖ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር። 27 በውስጠኛውም አደባባይ በደቡብ በኩል በር ነበረ፤ ከበር እስከ በር ድረስ በደቡብ በኩል መቶ ክንድ አድርጎ ለካ። 28 በደቡብም በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አገባኝ፤ እንደዚያውም መጠን አድርጎ የደቡብን በር ለካ፤ 29 እንደዚያውም መጠን አድርጎ የዕቃ ቤቶቹንና የግንቡን አዕማድ፥ መዛነቢያዎቻቸውንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 30 በዙሪያውም ደጀ ሰላሞች ነበሩ፤ ርዝመታቸውም ሃያ አምስት ክንድ፥ ወርዳቸውም አምስት ክንድ ነበረ። 31 መዛነቢያዎቹም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩ። 32 በውስጠኛውም አደባባይ በምሥራቅ በኩል አገባኝ፤ በሩንም ለካ፤ መጠኑም እንደ እነዚያ ነበረ። 33 እንደዚያም መጠን የዕቃ ቤቶቹንና የግንቡን አዕማድ፥ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 34 መዛነቢያዎቹም በስተ ውጭ ወደ አለው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። 35 በሰሜንም ወደ አለው በር አመጣኝ፤ እንደዚያውም መጠን ለካው፤ 36 የዕቃ ቤቶቹንና የግንቡን አዕማድ፥ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በዙሪያውም መስኮቶች ነበሩበት፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 37 የግንቡም አዕማድ ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያወጡ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። 38 በበሮቹም በግንቡ አዕማድ አጠገብ ዕቃ ቤቱና መዝጊያው ነበሩ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያጥቡ ነበር። 39 የሚቃጠለውንም መሥዋዕት፥ የኀጢአቱንና የበደሉንም መሥዋዕት ያርዱባቸው ዘንድ፥ በበሩ ደጀ ሰላም በዚህ ወገን ሁለት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ። 40 በሰሜን በኩል በአለው በር በስተውጭው፥ በመወጣጫው ደረጃዎች አጠገብ፥ በአንዱ ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ፤ በሌላውም ወገን በበሩ ደጀ ሰላም በኩል ሁለት ገበታዎች ነበሩ። 41 በበሩ አጠገብ በዚህ ወገን አራት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን አራት ገበታዎች ነበሩ፤ መሥዋዕት የሚያርዱባቸው ገበታዎች ስምንት ነበሩ። 42 ስለሚቃጠለውም መሥዋዕት ርዝመታቸው አንድ ክንድ ተኩል ወርዳቸውም አንድ ክንድ ተኩል ቁመታቸውም አንድ ክንድ የሆኑ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላውን መሥዋዕት የሚያርዱበትን ዕቃ ያኖሩባቸው ዘንድ፥ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ገበታዎች ነበሩ። 43 በዙሪያውም በስተውስጥ የነበረው የለዘበ ከንፈራቸው አንድ ጋት ነበረ፤ በገበታውም ላይ መክደኛ ነበረ፤ ከፀሐይና ከዝናምም የተሰወረ ነበረ። 44 ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፤ እነሆም ሁለት ቤቶች ነበሩ፤ አንዱ ወደ ሰሜን በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፤ መግቢያውም ወደ ደቡብ ይመለከት ነበረ፤ ሌላውም ወደ ደቡብ በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፤ መግቢያውም ወደ ሰሜን ይመለከት ነበር። 45 ሰውዬውም፥ “ይህ ወደ ደቡብ የሚመለከት ቤት ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው። 46 ወደ ሰሜንም የሚመለከተው ቤት መሠዊያዉን ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው፤ እነዚህ ከሌዊ ልጆች መካከል ያገለግሉት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ናቸው” አለኝ። 47 አደባባዩንም በአራት ማዕዘኑ ርዝመቱን መቶ ክንድ፥ ወርዱንም መቶ ክንድ አድርጎ ለካ፤ መሠዊያውም በቤቱ ፊት ነበረ። 48 ወደ ቤቱም ደጀ ሰላም አመጣኝ፤ የደጀ ሰላሙንም የግንብ አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን አምስት ክንድ፤ በዚያም ወገን አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ወርድ ዐሥራ አራት ክንድ ነበረ፤ በበሩም በዚህ ወገንና በዚያ ወገን የነበሩት ግንቦች ሦስት ሦስት ክንድ ነበሩ። 49 የደጀ ሰላሙም ርዝመት ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፥ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ዐሥር ደረጃዎች ነበሩ፤ አንድ በዚህ ወገን፥ አንድም በዚያ ወገን ሆነው በመቃኖቹ አጠገብ የግንብ አዕማድ ነበሩ። |