ሕዝቅኤል 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሕዝቅኤል የኢየሩሳሌምን በጠላት መከበብ እንደ አስረዳ 1 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ጡብን ወስደህ በፊትህ አኑራት፤ የኢየሩሳሌምንም ከተማ ሥዕል ሣልባት፤ 2 በውስጧም የሚዋጉበት ግንብን ሥራ፤ በሠራዊትም ክበባት፤ በዙሪያዋም ጦር አስፍር፤ የሚዋጋ ጦርንም ወደ አደባባይዋ ላክ። 3 የብረት ምጣድም ወስደህ በአንተና በከተማዪቱ መካከል ለብረት ቅጥር አድርገው፤ ፊትህንም ወደ እርስዋ አቅና፤ የተከበበችም ትሆናለች፤ አንተም ትከብባታለህ። ይህም ለእስራኤል ልጆች ምልክት ይሆናል። 4 “አንተም በግራ ጎንህ ተኛ፤ በምትተኛበትም ቀን ቍጥር የእስራኤልን ቤት ኀጢአት አኑርባት፤ ኀጢአታቸውንም ትሸከማለህ። 5 እኔም የኀጢአታቸውን ዓመታት ለአንተ የቀን ቍጥር እንዲሆንልህ ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ሰጥቼሃለሁ፤ የእስራኤልንም ቤት ኃጢአት ትሸከማለህ፤ 6 እነዚህንም በፈጸምህ ጊዜ በቀኝ ጎንህ ትተኛለህ፤ የይሁዳንም ቤት ኀጢአት አርባ ቀን ትሸከማለህ፤ አንዱን ቀን አንድ ዓመት አደረግሁልህ። 7 ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ፊትህን ታቀናለህ፤ ክንድህንም ታጸናለህ፤ በእርሷም ትንቢትን ትናገራለህ። 8 እነሆም ገመድ አደርግብሃለሁ፤ የምትከበብበትንም ወራት እስክትፈጽም ድረስ ከጎን ወደ ጎንህ አትገላበጥም። 9 “አንተም ስንዴንና ገብስን፥ አተርንና ባቄላን፥ ምስርንና አጃን ወደ አንተ ውሰድ፤ በአንድ ዕቃም ውስጥ አድርገህ እንጀራ ጋግር፤ በጎንህ እንደ ተኛህባት ቀን ቍጥር ሦስት መቶ ዘጠና ቀን ትበላዋለህ። 10 የምትበላውም በሚዛን በየቀኑ ሃያ ሃያ ሰቅል ይሁን፤ በየጊዜው ትበላዋለህ። 11 ውኃውንም በልክ የኢን መስፈሪያ ከስድስት እጅ አንድ እጅ ትጠጣለህ፤ በየጊዜው ትጠጣዋለህ። 12 የገብስ እንጎቻንም ትበላለህ፤ በሰው ኵስም ታበስለዋለህ፤ በፊታቸውም ታዳፍነዋለህ።” 13 እግዚአብሔርም፥ “እንዲሁ የእስራኤል ልጆች እነርሱን በምበትንባቸው በአሕዛብ መካከል ንጹሕ ያልሆነ እንጀራቸውን ይበላሉ” አለ። 14 እኔም፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ! ይህ አግባብ አይደለም፤ እነሆ ሰውነቴ አልረከሰችም፤ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጥንብና አውሬ የሰበረውን ከቶ አልበላሁም፤ ርኵስም ሥጋ በአፌ ውስጥ አልገባም” አልሁ። 15 እርሱም፥ “እነሆ በሰው ኵስ ፋንታ የከብት ኩበት ሰጥቼሃለሁ፤ በእርሱም እንጀራህን ትጋግራለህ” አለኝ። 16 ደግሞም እንዲህ አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! የኢየሩሳሌምን እንጀራ በትር እሰብራለሁ፤ በችግር እያሉ እንጀራን በሚዛን ይበላሉ፥ እየደነገጡም ውኃን በልክ ይጠጣሉ፤ 17 ይህም እንጀራንና ውኃን እንዲያጡ፥ እርስ በርሳቸውም እንዲገዳደሉ፥ በኀጢአታቸውም እንዲጠፉ ነው። |