ሕዝቅኤል 38 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጎግ የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆኖ እንደሚነሣ 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን በጎግ ላይና በማጎግ ምድር ላይ፥ በሮስ በሞሳሕና በቶቤል አለቃ ላይ አቅናበት፤ ትንቢትም ተናገርበት፤ 3 እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሮስ፥ የሞሣሕና የቶቤል አለቃ ጎግ ሆይ! እነሆ! እኔ በአንተ ላይ ነኝ። 4 እመልስህማለሁ፤ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ፤ አንተንና ሠራዊትህን ሁሉ፥ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፥ የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ጋሻና ራስ ቍርን፥ ሰይፍንም የያዙትን ሁሉ አወጣለሁ። 5 ፋርስንና ኢትዮጵያን፥ ሊብያንም፥ ከእነርሱ ጋር ጋሻና የራስ ቍርን የለበሱትን ሁሉ፥ 6 ጎሜርንና ከእርሱ ጋር ያሉትን ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻም ያለውን የቴርጋማን ቤትና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ ብዙዎችንም ሕዝቦች ከአንተ ጋር አወጣለሁ። 7 “አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ወገኖችህ ሁሉ ተዘጋጁ፤ አንተም ራስህን አዘጋጅተህ ጠባቂ ሁናቸው። 8 ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፤ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘለዓለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፤ እርስዋም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች፤ ሁሉም በሰላም ይቀመጡበታል። 9 እንደ ዝናም ትወጣለህ፤ እንደ ደመናም ምድርን ትሸፍን ዘንድ ትደርሳለህ፤ አንተም ከብዙ ሕዝብና ሠራዊት ጋር ትወድቃለህ።” 10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይገባል፥ ክፉ አሳብንም ታስባለህ፤ እንዲህም ትላለህ፦ 11 ወደ ጠፋች ሀገር እወጣለሁ፤ ተዘልለው በሰላም ወደሚኖሩ፥ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ፥ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡባት ምድር እገባለሁ፤ 12 ምርኮን ትማርክ ዘንድ፥ ብዝበዛንም ትበዘብዝ ዘንድ፥ ባድማም በነበሩ፥ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም በአገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትመልሳለህ። 13 ሳባና ድዳን፥ የተርሴስም ነጋዴዎች፥ መንደሮችዋም ሁሉ፦ ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ፥ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ፥ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ፥ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን? ይሉሃል።” 14 አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ ጎግንም እንዲህ በለው፥ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል በሰላም በተቀመጠ ጊዜ አንተ የምትነሣ አይደለምን? 15 አንተም፥ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ሁላቸው በፈረሶች ላይ የተቀመጡ፥ ታላቅ ወገንና ብርቱ ሠራዊት፥ ከሰሜን ዳርቻ ከስፍራችሁ ትመጣላችሁ። 16 ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፤ ጎግ ሆይ! በፊታቸው በተቀደስሁብህ ጊዜ፥ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አወጣሃለሁ። 17 “ጌታ እግዚአብሔር ለጎግ እንዲህ ይላል፦ በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ፥ በዚያች ዘመን ብዙ ዓመት ትንቢት በተናገሩ በባሪያዎች በእስራኤል ነቢያት እጅ በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን? 18 በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 19 በቅንአቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፦ በእርግጥ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤ 20 ከእግዚአብሔርም ፊት የተነሣ የባሕር ዓሣዎችና የሰማይ ወፎች፥ የምድረ በዳም አራዊት፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፤ ተራሮችም ይገለባበጣሉ፤ ገዳላገደሎችም ይወድቃሉ፤ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል። 21 በተራሮችም ሁሉ በእርሱ ላይ ፍርሀትን እጠራለሁ፤ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 22 በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍም፥ የበረዶም ድንጋይ፥ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ፥ ከእርሱም ጋር በአሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። 23 ታላቅ እሆናለሁ፤ እቀደስማለሁ፤ እመሰገናለሁም፤ በብዙ አሕዛብም ዐይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። |