ሕዝቅኤል 37 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ፤ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ፤ አጥንቶችም በሞሉበት ሸለቆ መካከል አኖረኝ። 2 በእነርሱም አንጻር በዙሪያቸው አዞረኝ፤ እነሆም በሜዳው እጅግ ነበሩ፤ እነሆም እጅግ ደርቀው ነበር። 3 እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን?” አለኝ። እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ታውቃለህ” አልሁ። 4 እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 5 ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ በእናንተ ላይ የሕይወትን መንፈስ አመጣለሁ። 6 ጅማትንም እሰጣችኋለሁ፤ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ፤ በእናንተም ላይ ቍርበትን እዘረጋለሁ፤ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” 7 እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ስናገርም ድምፅ ሆነ፤ እነሆም መናወጥ ሆነ፤ አጥንቶችንም እየራሱ በሆነ በሰውነቱ ከአጥንቶች ጋር አንድ አደረጋቸው። 8 እኔም አየሁ፤ እነሆም ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም ወጣ፤ ቍርበትም በላያቸው ተዘረጋ፤ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም። 9 እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገር፤ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፤ ለነፋስም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ! ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ እነዚህ ሙታን በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል” አለኝ። 10 እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንፋሽም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ። 11 እግዚአብሔርም ተናገረኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ አጥንቶች የእስራኤል ቤት ሁሉ ናቸው፤ እነሆ! አጥንቶቻችን ደርቀዋል፤ ተስፋችንም ጠፍቶአል፤ ፈጽመንም ተቈርጠናል ብለዋል። 12 ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ ሆይ! እነሆ መቃብራችሁን እከፍታለሁ፤ ከመቃብራችሁም አወጣችኋለሁ፤ ወደ እስራኤልም ምድር አገባችኋለሁ። 13 ሕዝቤ ሆይ! መቃብራችሁን በከፈትሁ ጊዜ፥ ከመቃብራችሁም በአወጣኋችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 14 መንፈሴንም በውስጣችሁ አሳድራለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ፤ በገዛ ምድራችሁም አኖራችኋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ተናገርሁ፥ እንዳደረግሁም ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።” የይሁዳና የእስራኤል መንግሥት አንድ ስለ መሆኑ 15 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 16 “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! አንድ በትር ውሰድና፦ ይሁዳንና ባልንጀሮቹን፥ የእስራኤልንም ልጆች በላዩ ጻፍ፤ ሌላም በትር ውሰድና፦ የኤፍሬም በትር ለዮሴፍና ለባልንጀሮቹ ለእስራኤል ቤት ሁሉ ብለህ በላዩ ጻፍ። 17 አንድ በትርም እንዲሆኑ አንዱን ከሁለተኛው ጋር ለአንተ አጋጥም፤ በእጅህም ውስጥ አንድ ይሁኑ። 18 የሕዝብህም ልጆች፦ ይህ የምታደርገው ነገር ምን ማለት እንደ ሆነ አትነግረንምን? ብለው በተናገሩህ ጊዜ፥ አንተ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 19 እነሆ በኤፍሬም እጅ ያለውን የዮሴፍን በትር ባልንጀሮቹንም የእስራኤልን ነገዶች እወስዳለሁ፤ ከእርሱም ከይሁዳ በትር ጋር አጋጥማቸዋለሁ፤ አንድ በትርም አደርጋቸዋለሁ፤ በእጄም ውስጥ አንድ ይሆናሉ በላቸው። 20 የምትጽፍባቸውም በትሮች በፊታቸው በእጅህ ውስጥ ይሆናሉ። 21 አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የእስራኤልን ልጆች ከገቡባቸው ከአሕዛብ መካከል እወስዳለሁ፤ ከስፍራም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ እስራኤልም ምድር አመጣቸዋለሁ፤ 22 በምድርም ላይ በእስራኤል ተራሮች ላይ አንድ ሕዝብ አደርጋቸዋለሁ፥ አንድ ንጉሥም በሁላቸው ላይ ይነግሣል፤ ከዚያ ወዲያ ሁለት ሕዝብ አይሆኑም፤ ከዚያ ወዲያም ሁለት መንግሥት ሆነው አይለያዩም። 23 ከዚያ ወዲያም በጣዖቶቻቸውና በርኵሰታቸው፥ በመተላለፋቸውም ሁሉ አይረክሱም፤ ኀጢአትም ከሠሩባት ዐመፅ ሁሉ አድናቸዋለሁ፤ አነጻቸውማለሁ፤ ሕዝብም ይሆኑኛል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ። 24 “ባሪያዬም ዳዊት በላያቸው ንጉሥ ይሆናል፤ ለሁሉም አንድ እረኛ ይሆንላቸዋል፤ በፍርዴም ይሄዳሉ ትእዛዜንም ይጠብቃሉ፤ ያደርጓትማል። 25 አባቶቻችሁም በኖሩባት፤ ለባሪያዬ ለያዕቆብ በሰጠኋት ምድር ይኖራሉ፤ እነርሱና ልጆቻቸው፥ የልጅ ልጆቻቸውም ለዘለዓለም ይኖሩባታል፤ ባሪያዬም ዳዊት ለዘለዓለም አለቃ ይሆናቸዋል። 26 የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፤ የዘለዓለምም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ እኔም እባርካቸዋለሁ፤ አበዛቸውማለሁ፤ መቅደሴንም ለዘለዓለም በመካከላቸው አኖራለሁ። 27 ማደሪያዬም በላያቸው ላይ ይሆናል፤ እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። 28 መቅደሴም ለዘለዓለም በመካከላቸው በሆነ ጊዜ፥ እኔ እስራኤልን የምቀድሰው እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።” |