ሕዝቅኤል 34 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የእስራኤል እረኞች 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገር፤ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፤ እረኞችንም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች ራሳቸውን ያሰማራሉን? እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? 3 ወተቱን ትጠጣላችሁ፤ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፤ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። 4 የደከመውን አላጸናችሁትም፤ የታመመውንም አልፈወሳችሁትም፤ የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም፤ የባዘነውንም አልመለሳችሁትም፤ የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም፤ በኀይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። 5 በጎችም እረኛን በማጣት ተበተኑ፤ ለዱርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ። 6 በጎች በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ በጎችም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚፈልግም አልነበረም፤ የሚመልስም አልነበረም። 7 “ስለዚህ እረኞች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ 8 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኞች ስለሌሉ፥ እረኞችም በጎችን ስላልፈለጉ፥ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎችን ስላላሰማሩ፥ በጎች ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎችም ለዱር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና፤ 9 ስለዚህ እረኞች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 10 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በእረኞች ላይ ነኝ፤ በጎችንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፤ በጎችንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ፤ ከዚያም ወዲያ እረኞች በጎችን አያሰማሩም፤ በጎችንም ከአፋቸው አድናለሁ፤ መብልም አይሆኑላቸውም። 11 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ራሴ በጎችን እሻለሁ፤ እጐበኛቸዋለሁም። 12 በደመናና በጭጋግ ቀን እረኛ ከበጎቹ መካከል የተለየውን እንደሚፈልግ፥ እንደዚሁ በጎችን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጭጋግ ቀን ከተበተኑባቸው ሀገሮች ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ። 13 ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ፤ ከሀገሮችም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ሀገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ፥ በፈሳሾችም አጠገብ፥ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩባት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ። 14 በመልካም ማሰማርያ አስማራቸዋለሁ፤ ጕረኖአቸውም በረዥሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጕረኖ ውስጥ ይመሰጋሉ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ። 15 እኔ ራሴ በጎችን አሰማራለሁ፤ አስመስጋቸውማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16 የጠፋውንም እፈልጋለሁ፤ የባዘነውንም እመልሳለሁ፤ የተሰበረውንም እጠግናለሁ፤ የደከመውንም አጸናለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውንም እጠብቃለሁ፤ በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።” 17 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እናንተም መንጋዬ ሆይ! እነሆ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል እፈርዳለሁ። 18 የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ የተሰማራችሁበት መልካሙ መሰማርያ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? 19 በጎችም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ፤ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ። 20 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ እነሆ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ። 21 እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው፥ የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥ 22 ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፤ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ። 23 በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ፤ እርሱም ያሰማራቸዋል፤ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ እረኛም ይሆናቸዋል። 24 እኔም እግዚአብሔር አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ ባሪያዬ ዳዊትም በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ። 25 “የሰላምንም ቃል ኪዳን ከዳዊት ቤት ጋር አደርጋለሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድር አጠፋለሁ፤ ተዘልለውም በምድረ በዳ ይኖራሉ፤ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ። 26 እነርሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች እባርካቸዋለሁ፤ ዝናቡንም በጊዜው አወርዳለሁ፤ የበረከትም ዝናብ ይሆናል። 27 የምድረ በዳ ዛፍም ፍሬውን ይሰጣል፤ ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፤ በምድራቸውም በሰላም ታምነው ይኖራሉ፤ የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ፥ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንኋቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 28 እንግዲህ ለአሕዛብ ንጥቂያ አይሆኑም፤ የምድርም አራዊት አይበሉአቸዋም፤ ተዘልለውም ይቀመጣሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም። 29 የሰላምን ተክል አቆምላቸዋለሁ፤ እንግዲህም ከራብ የተነሣ በምድር አያልቁም፤ የአሕዛብንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አይሸከሙም። 30 እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ፥ እነርሱም የእስራኤል ቤት ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 31 እናንተም በጎች፥ የማሰማሪያዬ በጎች፥ ሰዎች ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።” |