ሕዝቅኤል 33 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሕዝቅኤል የእስራኤል ጕበኛ 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ለሕዝብህ ልጆች ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጦርን በምድር ላይ በአመጣሁ ጊዜ፥ የምድር ሕዝብ ከመካከላቸው አንድ ሰውን ወስደው ለራሳቸው ጕበኛ ቢያደርጉ፥ 3 እርሱም በምድር ላይ የመጣውን ጦር በአየ ጊዜ መለከትን ቢነፋ፥ ሕዝቡንም ቢያስጠነቅቅ፤ 4 የመለከቱን ድምፅ የሚሰማ ሰው ባይጠነቀቅ፥ ጦር መጥቶ ቢወስደው፥ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል። 5 የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ስላልተጠነቀቀ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅስ ኖሮ ነፍሱን በአዳነ ነበር። 6 ጕበኛው ግን ጦር ሲመጣ ቢያይ፥ መለከቱንም ባይነፋ፥ ሕዝቡንም ባያስጠነቅቅ፥ ጦርም መጥቶ አንድ ሰው ከእነርሱ ቢወስድ፥ እርሱ በኀጢአቱ ተወስዶአል፤ ደሙን ግን ከጕበኛው እጅ እፈልጋለሁ። 7 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ቤት ጕበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ፤ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። 8 ኀጢአተኛውን፦ ኀጢአተኛ ሆይ! በርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ ኀጢአተኛውን ከክፉ መንገዱ ታስጠነቅቅ ዘንድ ባትናገር፥ ያ ኀጢአተኛ በኀጢአቱ ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። 9 ነገር ግን ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኀጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው፥ እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ፥ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን ታድናለህ። 10 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! የእስራኤልን ቤት፦ እናንተ፦ በደላችንና ኀጢአታችን በላያችን አሉ፤ እኛም ሰልስለንባቸዋል፤ እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው። 11 እኔ ሕያው ነኝና ኀጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኀጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! ተመለሱ፤ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ? በላቸው። 12 አንተም የሰው ልጅ ሆይ! የሕዝብህን ልጆች እንዲህ በላቸው፦ በበደለበት ቀን የጻድቅ ጽድቁ አያድነውም፤ ኀጢአተኛም ከኀጢአቱ በተመለሰበት ቀን በኀጢአቱ አይሰናከልም፤ ጻድቁም ኀጢአት በሠራበት ቀን በጽድቁ በሕይወት አይኖርም። 13 እኔ ጻድቁን፦ በርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ በጽድቁ ታምኖ ኀጢአት ቢሠራ በሠራው ኀጢአት ይሞታል እንጂ ጽድቁ አይታሰብለትም። 14 እኔም ኀጢአተኛውን፦ በርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ፥ እርሱ ከኀጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ቅን ነገርን ቢያደርግ፤ 15 ኀጢአተኛውም መያዣን ቢመልስ፥ የነጠቀውንም ቢከፍል፥ በሕይወትም ትእዛዝ ቢሄድ፥ ኀጢአትም ባይሠራ፥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም። 16 የሠራውም ኀጢአት ሁሉ አይታሰብበትም፤ ፍርድንና ቅን ነገርን አድርጎአልና፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። 17 “የሕዝብህ ልጆች፦ የእግዚአብሔር መንገድ የቀና አይደለም ይላሉ፤ ነገር ግን የእነርሱ መንገድ የቀና አይደለም። 18 ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአትን ቢሠራ ይሞትበታል። 19 ኀጢአተኛውም ከኀጢአቱ ተመልሶ ፍርድንና ጽድቅን ቢያደርግ በሕይወት ይኖርበታል። 20 እናንተ ግን፦ የጌታ መንገድ የቀና አይደለም ትላላችሁ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ! በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።” የኢየሩሳሌም መውደቅ 21 እንዲህም ሆነ፤ በተማረክን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር ከወሩም በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፦ ከተማዪቱ ተያዘች አለኝ። 22 ያመለጠውም ሳይመጣ በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረች፤ በነጋውም ወደ እኔ እስኪመጣ ድረስ አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተች፤ ከዚያም በኋላ እኔ ዲዳ አልሆንሁም። 23 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፥ 24 “የሰው ልጅ ሆይ! በእስራኤል ምድር በአሉ በባድማ ስፍራዎች የተቀመጡ፦ አብርሃም ብቻውን ሳለ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛም ብዙዎች ነን፤ ምድሪቱም ርስት ሆና ለእኛ ተሰጥታለች ይላሉ። ስለዚህ እንዲህ በላቸው፦ 25 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከደም ጋር ትበላላችሁ፤ ዐይናችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፤ ደምንም ታፈስሳላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? 26 ሰይፋችሁን ይዛችሁ ቆማችኋል፤ ርኩስ ነገርን ታደርጋላችሁ፤ የባልንጀሮቻችሁንም ሚስቶች ታስነውራላችሁ፤ በውኑ ምድሪቱን ትወርሳላችሁን? ስለዚህም እንዲህ በላቸው፦ 27 ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና በባድማ ስፍራዎች ያሉ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በምድረ በዳ ያለውን ለአራዊት መብል አድርጌ እሰጣለሁ፤ በአምባዎችና በዋሻዎች ያሉ በቸነፈር ይሞታሉ። 28 ምድሪቱንም ባድማና ውድማ አደርጋታለሁ፤ የኀይልዋም ስድብ ይቀራል፤ የእስራኤልም ተራሮች ባድማ ይሆናሉ፤ ማንም አያልፍባቸውም። 29 ስላደረጉትም ርኵሰት ሁሉ ምድሪቱን ባድማና ውድማ ባደረግሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 30 “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! የሕዝብህ ልጆች በቅጥር አጠገብና በቤት ደጆች ውስጥ ስለ አንተ ይናገራሉ፤ እርስ በርሳቸውም አንዱ ከአንዱ ጋር፦ እንሂድና እግዚአብሔር የሚለውን ቃል እንስማ ይላሉ። 31 ሕዝብ እንደሚመጣ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ እንደ ሕዝቤም በፊትህ ይቀመጣሉ፤ ቃልህንም ይሰማሉ፤ ነገር ግን አያደርጉትም፤ በአፋቸው ሐሰት ነገር አለና፥ ልባቸውም ጣዖታትን ይከተላልና። 32 እነሆ አንተ መልካም ድምፅ እንዳለው እንደሚወደድ መዝሙር ማለፊያም አድርጎ በገና እንደሚጫወት ሰው ሁነህላቸዋል፤ ቃልህንም ይሰማሉ ነገር ግን አያደርጉትም። 33 እነርሱም እንዲህ ይላሉ፦ እነሆ ይህ ይመጣል፤ በመጣም ጊዜ እነርሱ ነቢይ በመካከላቸው እንደ ነበረ ያውቃሉ።” |