ሕዝቅኤል 31 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ግብፅ በዝግባ ዛፍ እንደምትመሰል 1 እንዲህም ሆነ፤ በዐሥራ አንደኛው ዓመት በሦስተኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! የግብፅን ንጉሥ ፈርዖንንና ሕዝቡን እንዲህ በላቸው፦ በታላቅነትህ ማንን ትመስላለህ? 3 እነሆ አሦር ጫፉ እንደ ተዋበ፥ ችፍግነቱ ጥላ እንደ ሰጠ፥ ቁመቱም እንደ ረዘመ፥ ራሱም ወደ ደመናዎች እንደ ደረሰ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ነበረ። 4 ውኃም አበቀለው፥ ቀላይም አሳደገው፥ ወንዞችም በተተከለበት ዙሪያ ይጎርፉ ነበር፤ ፈሳሾቹንም ወደ ምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ ላከ። 5 ስለዚህ ቁመቱ ከምድረ በዳ ዛፍ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ አለ፤ ቅርንጫፎቹም በዙ፤ ጫፎቹም ከብዙ ውኆች የተነሣ ረዘሙ። 6 የሰማይም ወፎች ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ተዋለዱ፤ የምድርም አራዊት ሁሉ ከጫፎቹ በታች ተዋለዱ፤ ከጥላውም በታች ታላላቆች አሕዛብ ሁሉ ይቀመጡ ነበር። 7 ሥሩም በብዙ ውኃ አጠገብ ነበረና በታላቅነቱና በጫፎቹ ርዝመት የተዋበ ነበረ። 8 በእግዚአብሔር ገነት የነበሩ ዝግባዎች አይተካከሉትም፥ ጥዶችም ቅርንጫፎቹን፥ አስታ የሚባለውም ዛፍ ጫፎቹን አይመሳሰሉትም ነበር፤ የእግዚአብሔርም ገነት ዛፍ ሁሉ በውበቱ አይመስለውም ነበር። 9 በጫፎቹ ብዛት ውብ አደረግሁት፤ በእግዚአብሔርም ገነት በዔድን የነበሩ ዛፎች ሁሉ ቀኑበት። 10 “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቁመትህ ከፍ ከፍ ብሎአልና፥ ራስህም በደመናት መካከል ደርሶአልና፤ ትዕቢቱንም አየሁ፤ 11 በአሕዛብም አለቆች እጅ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ እርሱም እንደ ክፋቱ መጠን ያደርግበታል፤ እኔም አሳድደዋለሁ። 12 የሌላ ሀገር ሰዎች፥ የአሕዛብ ጨካኞች የሆኑ፥ ቈርጠው ጣሉት፤ በተራሮችና በሸለቆዎች ሁሉ ውስጥ ጫፎቹ ወደቁ፤ ቅርንጫፎቹም በምድር ፈሳሾች ሁሉ ላይ ተሰባበሩ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ከጥላው ተመልሰው ተዉት። 13 በወደቀው ግንድ ላይ የሰማይ ወፎች ሁሉ ይቀመጣሉ፤ የምድርም አራዊት ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ይሆናሉ። 14 በውኃው አጠገብ ያሉ የዕንጨቶች ሁሉ ቁመት እንዳይረዝም ራሱም ወደ ደመና እንዳይደርስ ያንም ውኃ የሚጠጡት እንጨቶች ሁሉ በርዝመታቸው ከእርሱ ጋራ እንዳይተካከሉ ሁሉም ወደ መቃብር በሚወርዱ ሰዎች መካከል በጥልቅ ምድር ሞቱ። 15 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ሲኦል በወረደበት ቀን ልቅሶን አስለቀስሁ፤ ቀላዩንም ስለ እርሱ ሸፈንሁት፤ ፈሳሾችንም ከለከልሁ፤ ታላላቆችም ውኆች ተከለከሉ፤ ሊባኖስንም ስለ እርሱ አሳዘንሁት። የዱርም ዛፎች ሁሉ ስለ እርሱ ዛሉ። 16 ወደ ጕድጓድ ከሚወርዱ ጋር ወደ ሲኦል በጣልሁት ጊዜ ከመውደቁ ድምፅ የተነሣ አሕዛብን አንቀጠቀጥሁ፤ ውኃም የሚጠጡ ሁሉ፥ ምርጦችና መልካሞች የሊባኖስ ዛፎች፥ የዔድን ዛፎች ሁሉ በታችኛው ምድር ውስጥ ተጽናንተዋል። 17 እነርሱም በሰይፍ ወደ ተገደሉት ወደ ሲኦል ከእርሱ ጋር ወረዱ፤ በጥላው ሥር ይኖሩ የነበሩ ዘሮቹም በአሕዛብ መካከል ጠፉ። 18 “በክብርና በታላቅነት በዔድን ዛፎች መካከል ማንን ትመስላለህ? ነገር ግን ከዔድን ዛፎች ጋር ወደ ታችኛው ምድር ያወርዱሃል፤ በሰይፍም በተገደሉት ባልተገረዙት መካከል ትተኛለህ። ይህም ፈርዖንና የሕዝቡ ብዛት ሁሉ ነው፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። |