ሕዝቅኤል 30 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ጌታ ግብፅን እንደሚቀጣ 1 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ! 3 ቀኑ ቅርብ ነው፤ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፤ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ማለቂያ ጊዜ ይሆናል። 4 ሰይፍ በግብፅ ላይ ይመጣል፤ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፤ የተገደሉትም በግብፅ ውስጥ ይወድቃሉ፤ ብዛቷንም ይወስዳሉ፤ መሠረቷም ይፈርሳል። 5 ኢትዮጵያና ፉጥ፥ ሉድም፥ ዓረብም ሁሉ፥ ኩብም፤ ሊብያም፤ ቀርጤስም የተደባለቀ ሕዝብም ሁሉ፥ ቃል ኪዳንንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ። 6 “እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ ግብፅን የሚደግፉ ይወድቃሉ፤ የኀይልዋም ትዕቢት ይወርዳል፤ ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሰዌኔ ድረስ በእርስዋ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 7 ባድማም በሆኑ ሀገሮች መካከል ባድማ ይሆናሉ፤ ከተሞችዋም በፈረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ። 8 እሳትንም በግብፅ ላይ በአነደድሁ ጊዜ፥ ረዳቶችዋም ሁሉ በተሰበሩ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 9 በዚያ ቀን መልእክተኞች ተዘልለው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማጥፋት ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ፤ በግብፅም ቀን ሁከት ይሆንባቸዋል፤ እነሆ፥ ይመጣልና። 10 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የግብፅን ብዛት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አጠፋለሁ። 11 እርሱና ሕዝቡ የአሕዛብም ኀያላን ምድሪቱን ለማጥፋት ይላካሉ፤ ግብፃውያንንም በሰይፍ ይወጉአቸዋል፤ ምድሪቱም በሙታን ትሞላለች። 12 ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋለሁ፤ ምድሪቱንም በክፉ ሰዎች እጅ እሰጣለሁ፥ ምድሪቱንና ሞላዋንም በባዕዳን እጅ ባድማ አደርጋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ። 13 “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣዖቶቹን አጠፋለሁ፤ ምስሎቹንም ከሜምፎስ እሽራለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያም በግብፅ ምድር አለቃ አይሆንም፤ በግብፅ ምድር ላይም ፍርሀትን አደርጋለሁ። 14 ጳትሮስንም አፈርሳለሁ፤ በጣኔዎስም ላይ እሳትን አነድዳለሁ፤ በዲዮስጶሊን ላይም ፍርድን አደርጋለሁ። 15 በግብፅም ኀይል በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፤ የሜምፎስንም ብዛት አጠፋለሁ። 16 በግብፅም ላይ እሳትን አነድዳለሁ፤ ሲንም ትታወካለች፤ ኖእም ትሰበራለች፤ ሜምፎስም ምድረ በዳ ትሆናለች። 17 የሄልዮቱ ከተማና የቡባስቱም ጐልማሶች በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ሴቶችም ይማረካሉ። 18 የግብፅን ቀንበር በዚያ በሰበርሁ ጊዜ በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል፤ የኀይልዋም ትዕቢት ይጠፋባታል፤ ደመናም ይጋርዳታል፤ ሴቶች ልጆችዋም ይማረካሉ። 19 እንዲሁ በግብፅ ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” 20 እንዲህም ሆነ፤ በዐሥራ አንደኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21 “የሰው ልጅ ሆይ! የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬአለሁ፥ እነሆም ይድን ዘንድ መድኃኒት ቀብተው አያደርቁትም፤ ሰይፉንም ለመያዝ ኀይልን ያገኝ ዘንድ አልታሰረም። 22 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ነኝ የጸናችውንና የተሰበረችውንም ክንዱን እሰብራለሁ፤ ሰይፉንም ከእጁ አስጥለዋለሁ። 23 ግብፃውያንንም በአሕዛብ መካከል እበትናለሁ፤ በሀገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ። 24 የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ፤ ሰይፌንም በእጁ እሰጣለሁ፤ ግብፅንም ይወጋበታል፥ ምርኮዋንም ይማርካል፤ ሰለባዋንም ይሰልባል። 25 የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አጸናለሁ፤ የፈርዖንም ክንድ ይወድቃል፤ ሰይፌንም በባቢሎን ንጉሥ እጅ በሰጠሁ ጊዜ፥ እርሱም በግብፅ ምድር ላይ በዘረጋው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 26 ግብፃውያንንም በአሕዛብ መካከል እበትናለሁ፤ በሀገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ፤ ሁሉም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” |